ቀጥታ፡

ኢትዮ ቴሌኮም ቴክኖሎጂን ከማስፋፋትና ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ይወጣል

ባህር ዳር፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ)፡- ኢትዮ ቴሌኮም ቴክኖሎጂን ከማስፋፋትና ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።

ኢትዮ ቴሌኮም በአማራ ክልል ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የሚውል 1 ሺህ 200 ደርዘን የመማሪያ ደብተር ድጋፍ አድርጓል።


 

በኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ምዕራብ ሪጅን ኦፕሬሽን ዳይሬክተር አቶ አበበ ጥሩነህ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮ ቴሌኮም ቴክኖሎጂን ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።

በዛሬው ዕለትም 1.5 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የመማሪያ ደብተሮች በአማራ ክልል ለሚገኙ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

በድጋፉ ተጠቃሚ የሚሆኑትም በባህር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች የሚገኙ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ቀደም ሲልም ከ18 ሺህ ደርዘን ደብተር ቤተሰቦቻቸው አነስተኛ ገቢ ላላቸው ተማሪዎች ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፤ ይህንኑ በጎ ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።


 

የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ፍሬሰላም ዘገዬ በበኩላቸው፤ ድጋፉ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በትምህርት ቁሳቁስ ዕጥረት ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይሆኑ የሚያግዝ ነው።

ኢትዮ ቴሌኮም ከፌዴሬሽኑ ጋር ተቀራርቦ በመስራት የአካል ጉዳተኞችን ችግር እያቃለለ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ቀደም ሲል በክልሉ ለሚገኙ ከ15 ሺህ የሚበልጡ አካል ጉዳተኞች ተጠቃሚ ማድረጉንም አመልክተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም