የግብፅ የውሃ አባካኝነት እና ያረጀው የቅኝ ግዛት እሳቤ - ኢዜአ አማርኛ
የግብፅ የውሃ አባካኝነት እና ያረጀው የቅኝ ግዛት እሳቤ
ግብፅ ለዓባይ ወንዝ ፍሰት ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ የሌላት ብትሆንም፣ የዓባይን ውኃ በማባከን ትታወቃለች። ይህ በዓባይ ወንዝ እውነት ላይ ያለ አስገራሚ ተቃርኖ ነው።
በርካታ የውሃ ሃብት ተንታኞችና ድንበር ተሻጋሪ የውኃ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፤ በግብፅ ግድቦች ውስጥ የሚከማቸው ውኃ ሀገሪቱ ባላት እጅግ ሞቃታማ የአየር ንብረት ምክንያት በትነት ይባክናል።
የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የድንበር ተሻጋሪ ውኃዎች እና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ (GERD) አማካሪ ቡድን ሰብሳቢ፣ እንዲሁም የምሥራቅ ናይል አህጉራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ እንደሚገልጹት፣ የታላቁ አስዋን ግድብ የፈጠረው የናስር ሀይቅ የሚገኘው በዓለም ላይ በጣም ሞቃት እና ደረቅ ከሆኑት የሰሃራ በረሃ ክፍሎች ውስጥ ነው። በዚህም አስዋን ግድብ በየዓመቱ በትነት ምክንያት ብቻ ከ15 እስከ 16 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ያጣል።
ከዚህ በተጨማሪ በግብፅ የዓባይ ሸለቆ እና ዴልታ አሁንም ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የግብርና መሬት የሚጠጣው በባህላዊ የጎርፍ/የቦይ መስኖ ዘዴ ነው።
ይህም ከ40 እስከ 50 በመቶ የሚሆነውን በትነት፣ በመሬት ሰርገት እና ባልተጣጠመ ስርጭት ምክንያት ያባክናል። በግብጽ እንደ ጠብታ መስኖ እና ረጭ መስኖ (Sprinkler) ያሉ ዘመናዊና ውሃ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎች ትግበራ አሁንም አነስተኛ ነው።
በሌላ በኩል በረሃን ወደ እርሻ መሬት ለመቀየር የተቀረፁ ትልልቅ ፕሮጀክቶች በረጅም ክፍት ካናሎች ውሃን ወደ በረሃ በመሳብ ለማልማት የሚደረገው ጥረት፣ ውሃው ክፍት በሆኑ ካናሎች በሚጓዝበት ወቅት በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት በትነት እና ወደ አሸዋማ መሬት በመስረግ ከፍተኛ ውሃም ለዘመናት እያባከነች ትገኛለች።
ይህ አልበቃት ብሎ ግብፅ በደረቅና ከፍተኛ የትነት መጠን ባላቸው አካባቢዎች ከፍተኛ የውሃ ፍጆታ ያላቸውን ሰብሎች በስፋት ታመርታለች።
እንደ ሩዝ እና የሸንኮራ አገዳ ያሉ ከፍተኛ ውሃ የሚፈልጉ ሰብሎችን በበረሃማ የአየር ጠባይ ውስጥ በጎርፍ መስኖ ማልማት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሜትር ኪዩብ ውሃን ታባክናለች።
በተቃራኒው ውኃን በኢትዮጵያ ጥልቅ፤ ጠባብ ሸለቆዎች ውስጥ እና አመቺ የአየር ንብረት ባለበት አካባቢ ማከማቸት የትነት መጠንን ለመቀነስ እጅግ ከፍተኛ ሚና አለው።
ዋናው የውኃ ማከማቻ በኢትዮጵያ መሆኑ በሙቀት ሊባክን የሚችለውን በርካታ መጠን ያለው ውኃ ከማዳኑም በላይ፣ ወደ ታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚለቀቀውን የውኃ መጠን አስተማማኝና የተረጋጋ እንዲሆን ያደርገዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚገኝበት ቦታ ቀዝቃዛና ጥልቅ ሸለቆ በመሆኑ፣ ውሃን በከፍተኛ ሙቀት ውስጥ ከሚገኘው የአስዋን ግድብ ይልቅ እዚያ መያዝ በትነት የሚባክነውን የውሃ መጠን በእጅጉ ይቀንሳል። ይህም ለግብፅም ጭምር ውሃን የሚቆጥብ ሳይንሳዊ እውነታ ነው።
ሳይንሳዊ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ግብፅ አሁንም ያረጀና የፈጀ የቅኝ ግዛት እሳቤን በመያዝ በዓባይ ወንዝ ላይ የተሳሳተ አቋም ማራመዷን ቀጥላለች።
ግብፅ አሁንም በ1929 እና 1959 በቅኝ ግዛት ዘመን በተደረጉ፣ ኢትዮጵያን ያገለሉ ፍትሃዊ ያልሆኑ ውሎች ላይ በመመስረት የከልካይነት መብት አለኝ የሚል ጊዜ ያለፈበት እሳቤ ለማራማድ እየጣረች ነው።
የኢትዮጵያን ዕድገትና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ለግብፅ እንደ ስጋት አድርጎ በመሳል፣ የዓባይን ጉዳይ የደህንነት ስጋት በማስመሰል ጫና ለመፍጠር የምታደረግው ከንቱ ሙከራም ከዚህ ካረጀ እሳቤ የመነጨ ነው።
ነገር ግን ካይሮ በኢትዮጵያ ሉዓላዊ መብት ላይ ጫና ለማሳደር ከምታደርገው ከንቱ ጥረት ይልቅ፣ የራሷን የውሃ አጠቃቀም ማዘመን፣ ዘመናዊ የመስኖ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እና ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ጥቅም እና በመከባበር ላይ የተመሠረተ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ትብብር ማድረግ የረጅም ጊዜ መፍትሔ ነው።