ቀጥታ፡

የከምባታ ዘመን መለወጫ በዓል "መሳላ" በአብሮነትና በትብብር የመሥራት እሴት ጎልቶ የሚታይበት በዓል ነው- አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ

ዱራሜ ፤ መስከረም  12/2019(ኢዜአ) ፦የከምባታ ዘመን መለወጫ በዓል "መሳላ" በአብሮነትና በትብብር የመሥራት እሴት ጎልቶ የሚታይበት በዓል መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ ገለፁ። 

የከምባታ ዘመን መለወጫ "መሳላ" በዓል በዱራሜ ሁለገብ ስታዲየም በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።


 

ዋና አፈ ጉባኤዋ በወቅቱ እንዳሉት፤ የከምባታ ዘመን መለወጫ በዓል "መሳላ" በአብሮነትና በትብብር የመሥራት እሴት ጎልቶ የሚታይበት በዓል ነው።

"መሳላ" የመደጋገፍና የአንድነት እሴቶችን ከማጠናከር ባለፈ ለክልሉ ልማትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማዋል እንደሚገባ አመልክተዋል።

በዓሉ ወደ አዲስ ዘመን የመሻገር ምልክት ከመሆኑም በተጨማሪ ባህላዊ ክዋኔዎቹ፣ የመደጋገፍና የአብሮነት እሴት ጎልቶ የሚታይበት ነው ብለዋል።

እንዲሁም የተጣሉ የሚታረቁበት፣ የተራራቁ የሚቀራረቡበት በመሆኑ እሴቱን አስጠብቆ ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም አስገንዘበዋል።


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ በበኩላቸው፤ የ"መሳላ" በዓል ከክረምት ወቅት ወደ ሌላ የመሻገር ምልክት ብቻ ሳይሆን የመተሳሰብና የመደጋገፍ እሴት የሚጎለብትበት መሆኑን ተናግረዋል።

በዓሉ ጥላቻና ቂምን በማስወገድ ሰላምን በማፅናት፣ በአብሮነትና በመረዳዳት የሚከበር መሆኑንም አክለዋል።


 

የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሸቱ፤ "መሳላ" የአዲስ እሳቤ ማስጀመሪያ በመሆኑ በተለየ መንገድ በድምቀት የሚከበር በዓል ነው ብለዋል።

የበዓሉን እሴቶች በማጎልበት ለሕዝቦች አንድነት መጠናከር ለማዋል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በበዓሉ አከባበር ላይ የክልሉ፣ የዞንና የዱራሜ ከተማ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የባህል ሽማግሌዎችና ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ተጋባዥ እንግዶች ታዳሚ ሆነዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም