ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል በኢንዲስትሪ ልማት፣ በአገልግሎት አሰጣጥና በኮሪደር ልማት የተከናወኑ ተግባራት ተሞክሮ የሚወሰድባቸው ናቸው

ሐረር፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ):-በሐረሪ ክልል በኢንዲስትሪ ልማት፣ በአገልግሎት አሰጣጥና በኮሪደር ልማት የተከናወኑ ተግባራት ተሞክሮ የሚወሰድባቸው መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አመራር አካላት ገለጹ። 

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማና የኢንዱስትሪ ክላስተር አስተባባሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤልን ጨምሮ የክልሉ አመራር አካላት በሐረሪ  የተከናወኑ የኮሪደር ልማት፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ ኢንዱስትሪ ልማት እና ሌሎች ስራዎችን ጎብኝተዋል።


 

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማና የኢንዱስትሪ ክላስተር አስተባባሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል በሀረሪ ክልል በኢንዱስትሪ ዘርፍ ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጪ ምንዛሬን የማስቀረት ስራ በስፋት ስለመከናወኑ መመልከታቸውን ተናግረዋል።


 

በዚህም ኢንዱስትሪው የሚያመርተው የመብራት ምሰሶ ለኮሪደር ልማት ስራ በማዋል ከተማዋን ውብና ማራኪ ማድረጉን በምልከታቸው ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል።

በክልሉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዜጎች በአንድ ቦታ የተለያዩ አገልግሎት በማግኘት ወጪና ጊዜን ባግባቡ እንዲጠቀሙ እያደረገ መሆኑን መመልከታቸውን ተናግረዋል።

በአካባቢው የሚገኙ ሃብትንና ጥበብን በመጠቀም የሚገነቡት የገጠር ሞዴል መንደሮችም የሚበረታቱ መሆኑንም አንስተዋል።

እንደ አቶ ስንታየሁ ገለጻ በክልሉ በኢንዲስትሪ ልማት፣ በአገልግሎት አሰጣጥና በኮሪደር ልማት የተከናወኑ ተግባራት ተሞክሮ የሚወሰድባቸው ናቸው።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ናትናኤል ሚሊዮን በበኩላቸው በክልሉ ጥንታዊ እና ታሪካዊ እሴቶችን በያዘ መልኩ የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች ሳቢና ማራኪ ናቸው ።


 

በመሰረተ ልማት ግንበታ፣  በኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት አሰጣጥ  ቴክኖሎጂን በመጠቀም   የሚከናወኑ ተግባራት ዓርዓያነት ያላቸውና  ተጠናክረው ሊቀጥሉ የሚገቡ ናቸው ብለዋል።

በጉብኝቱ ላይ የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር እና ሌሎች የክልሎቹ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም