በደም መፍሰስ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን መጠን ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ የሚያስችሉ አሰራሮች ተዘርግተዋል - ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በደም መፍሰስ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን መጠን ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ የሚያስችሉ አሰራሮች ተዘርግተዋል - ጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ)፦ከወሊድ በኋላ በደም መፍሰስ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን መጠን ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ የሚያስችሉ አሰራሮች በጤና ተቋማት መዘርጋታቸውን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ገለጹ።
የጤና ሚኒስቴር ሀገር አቀፍ የሁለተኛው ብሔራዊ ከወሊድ በኃላ የሚከሰት የደም መፍሰስ እና የእናቶች ጤና ፖሊሲ ሰነድ ላይ ያተኮረ ምክክር "ከቃል ኪዳን ወደ ተግባር" በሚል መሪ ሃሳብ እያካሄደ ይገኛል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በዚህ ወቅት፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በመደመር እሳቤ በሁሉም መስክ በከፍተኛ የብልፅግና ጉዞ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።
በጤናው ዘርፍም በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን አንስተው፤ይህም በሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ የተገኘ ነው ብለዋል።
በሚኒስቴሩ እና በሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ በተሰራው ስራ የእናቶች ሞት መጠን በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ መጠን መቀነስ መቻሉን አንስተዋል።
ይህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሀገራት የእናቶችና ህጻናት ሞት ቅነሳ ላይ በትኩረት ከሚሰሩ ቀዳሚ ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ያስቻለ መሆኑን በመግለጽ።
በቀጣይ በ2030ዓም ይህን የእናቶች የሞት መጠን መቀነስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንና ለስኬታማነቱም በሚቀጥሉት 3 እና 4 ዓመታት ከፍተኛ ሥራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ለዚህም ከወሊድ በኋላ በደም መፍሰስ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን መጠን ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ የሚያስችሉ አሰራሮች በጤና ተቋማት መዘርጋታቸውን ተናግረዋል።
መድረኩ የተዘጋጀው የእናቶች እና የሕፃናት ጤናን የበለጠ ለማሻሻል፣ እስካሁን ያሉትን ስኬቶች እንደ ወረት ለመውሰድ፣ ቀሪ ስራዎችን ደግሞ በመገምገም የማሻሻያ ተግባራት ማከናወን የሚያስችሉ ፖሊሲዎችንና ሰነዶችን ይፋ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
የፖሊሲ ሰነዶቹ የጤና ባለሙያዎች የበረታ የደም መፍሰስን በጊዜ ለይተው ወደሚቀጥለው ተቋም ሪፈር ማድረግና አስፈላጊው ግብዓት እንዲሟላ ማድረግ የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል።
በተጨማሪም እናቶች ሙሉ በሙሉ በጤና ተቋማት መቆየት እንዲችሉ የምክር አገልግሎት የሚሰጡበት መሆኑን ጠቁመው
ለፖሊሲው ተግባራዊነት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።