ቀጥታ፡

የዓባይ እናት ኢትዮጵያ የጠላትን ሰንሰለት እየበጣጠሰች ጉዞዋን ትቀጥላለች

86 በመቶ የሚሆነውን የዓባይ ውሃ አመንጭታ የምታፈሰው ኢትዮጵያ ለዘመናት ልጆቿ በጥም፣ በጨለማና በድህነት ሲማቅቁ ዝም ብላ እንድታይ ተፈርዶባት ነበር።

በአንጻሩ በዓለም አቀፍ መድረኮች «የውሃ እጥረት ስጋት አለብኝ» እያለች የምትለፈልፈው ካይሮ፣ ተበዳይ መስሎ የመቅረብ ትርክቷ ከጀርባ ያለውን እውነተኛ የስግብግብነትና የቀጣናዊ የበላይነት ፍላጎት ለመሸፈን የተበጀ ጊዜ ያለፈበት ጭንብል ነው።

ካይሮ ውሃ እያባከነች፣ ኢትዮጵያውያን የጓሮ አትክልት እንዳያለሙ ለመከልከል ተሞክሯል። ያ የጠላት ሰንሰለት ግን በሕዳሴ ግድብ ተበጣጥሷል።

በነገራችን ላይ ግብፅ ለምዕተ ዓመታት የሚበቃት ግዙፍ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት አላት። በኢትዮጵያ ለብዙ ዓመታት ዝናብ ቢቋረጥ እንኳ የማይነጥፍ ተፈጥሯዊ የውሃ ክምችት ይዛ ሳለች፣ የዓባይን ውሃ በግዴለሽ አጠቃቀም ታባክናለች። ይህ ደግሞ ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው።

በየበረሃው ቅንጦተኛ ሰፊ ረግረጋማ መሬት እንዳላት በማስመሰል ከፍተኛ ውሃ የሚጠቀሙትን ሸንኮራ አገዳና ሩዝ ታመርታለች።

አዳዲስ የቅንጦት ከተሞችንና የመዝናኛ ገንዳዎችን እየገነባች ውሃ ታባክናለች። በሌላ በኩል ግን ኢትዮጵያውያን ለዕለት ጉርሳቸውና ለቤታቸው መብራት እንኳ ወንዞቻቸውን እንዳያለሙ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ያለማቋረጥ ትነዛለች።

ሌሎች የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት በድህነት እንዲማቅቁም ቀን ከሌሊት ታሴራለች። በዚህም ግብፅ የራሷን የቅንጦት አኗኗር እያስፋፋች የሌሎችን ህልውና ለማነቅ ከምታደርገው የሚልቅ ፍርደ ገምድልነት የለም።

የዓባይን ውሃ ፍሰት ለመጠበቅ ከ50 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን እየተከለች ያለችውን ኢትዮጵያን ማመስገን ሲገባት፣ የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት ለማናጋት የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም።

ቅጥረኞችን በመጠቀም ሱዳንን ለማፍረስና ኢትዮጵያን የማዳከሚያ መተላለፊያ ለማድረግ ትሰራለች። በቀይ ባሕር አካባቢ ያለ ማንኛውም ሀገር እንዲበለጽግና እንዲያድግ አትፈልግም። ለዚህም ባንዳ እየመለመለች የቀጣናው ሰላም ዋና ጠንቅና የጥፋት መሪ ሆናለች።

ኢትዮጵያን ጨምሮ የላይኛው የወንዙ ተፋሰስ ሀገራት በሉዓላዊ ሀብታቸው ላይ መወሰንና ማልማት ጀምረዋል። ይህ ደግሞ ውሃ አባካኝነቷን የረሳችውን ግብፅ የጣረ ሞት ጩኸትና ቅዠት ውስጥ ከቷታል። የውሃ ሚኒስትሯና ሌሎች የዘርፉ ሃላፊዎች ደግሞ ሙሾ አውራጅ ሆነው መጥተዋል።

ለዓባይም ሆነ ለናይል ጠብታ አበርክቶ የሌላት ግብፅ የላይኛውን ተፋሰስ ማለትም የወንዙን መፍለቂያ ሀገራትን ሳታስፈቅድ አስዋንን የገነባችው ካይሮ፣ ዛሬ በሰው ቤት ፈትፋች ልሁን፣ ግድብ ስትገነቡም እኔን ፈቃድ ጠይቁ ብትልም፤ ጊዜውም ሁኔታውም አልፈቀዱም ወደፊትም አይፈቅዱም። ጭንብሏም ካባዋም ከላይዋ ላይ እየወለቁ የእውነትና የፍትሕ መንገድ እየተጠረገ መጥቷል።

የኢትዮጵያ የመልማት እቅድና የተፈጥሮ ሃብቷን የመጠቀም ጽኑ ፍላጎት በምንም ዓይነት የዛቻና የከሰረ ፕሮፓጋንዳ ጋጋታ አይገታም።

ጊዜው ተቀይሯል፤ የኃይል ሚዛኑም በጽናትና በፍትሃዊነት ተተክቷል። የዓባይ እናት በልማት ሰልፍ ላይ ናት። የሕዳሴ ግድብ ደግሞ በዓባይ ላይ የመጀመሪያው ሆኗል። ይቀጥላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም