በአማራ ክልል ገቢን አሟጦ የመሰብሰብ አቅምን ለማሳደግ ርብርብ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ገቢን አሟጦ የመሰብሰብ አቅምን ለማሳደግ ርብርብ እየተደረገ ነው
ባህር ዳር፤ መስከረም 12/2019(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማስፋት የገቢ አሰባሰብ አቅምን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።
በአማራ ክልል ባለፉት ሁለት ወራት ከ18 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ከተለያዩ የገቢ ምንጮች መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው የግብር ትምህርትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ታዘባቸው ጣሴ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የገቢ አሰባሰብ አቅምን ከፍ በማድረግ በራስ አቅም የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
በተለይም ክልሉ የሚያመነጨውን ኢኮኖሚ የሚመጥን ገቢ ያለምንም ማንጠባጠብ ለመሰብሰብ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት የመዘርጋት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች ከ166 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን፣ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ከ18 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።
ቀሪውን ዕቅድ ለማሳካትም አዳዲስ ግብር ከፋዮችን ወደ ግብር መረብ ከማስገባት ባሻገር ገቢ የመሰብሰብ አቅምን የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በክልሉ ገቢ የመሰብሰብ አቅምን በማሳደግ በራስ አቅም የሕዝብን መሠረታዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የመመለስና የመሥራት ልምድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም አብራርተዋል።
ህብረተሰቡ ለገዛው ዕቃና ላገኘው አገልግሎት ደረሰኝ የመቀበልና የመጠየቅ ልማድን በማዳበር የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
ቢሮው በቀጣይም የግብር አሰባሰብ ሂደቱን ይበልጥ ዘመናዊ፣ ፍትሐዊና ቀልጣፋ በማድረግ ክልሉ የሚያመነጨውን ኢኮኖሚ የሚመጥን ገቢ ለመሰብሰብ ጠንክሮ እንደሚሠራ ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።
በክልሉ ባለፈው በጀት ዓመት በተከናወነ የገቢ አሰባሰብ ሂደት ከ93 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሎ እንደነበርም ከዳይሬክተሩ ገለጻ ለማወቅ ተችሏል።