ቀጥታ፡

"ማሽቃሮ" የአብሮነት መገለጫ ነው - ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

ቦንጋ፣ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ)፦ የካፋ ዘመን መለወጫ  "ማሽቃሮ" በአል አብሮነት የሚጠናከርበትና በጋራ የተሻለ ለመስራት  የሚታቀድበት መሆኑን  የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)  ገለጹ።

የካፋ ዘመን መለወጫ የ"ማሽቃሮ" በአል በቦንጋ ከተማ በቦንጊ ሸምበቶ የበአሉ መክበሪያ   ስፍራ በድምቀት ተከብሯል።


 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት የካፋ ዘመን መለወጫ "ማሽቃሮ" ወንድማማችነት የሚጎለብትበትና አብሮነት የሚጠናከርበት በዓል ነው  ። 

በዓሉ በአብሮነትና በሰላም  አዲስ አመትን በመቀበል  የተሻለ ለመስራት  የሚታቀድበት መሆኑን ተናግረዋል ።

የ"ማሽቃሮ" በዓል የአዝመራ  መድረስን ተከትሎ  በአብሮነትና በፍቅር የሚከበር  መሆኑንም አመልክተዋል።


 

ይህም ባህላዊ  ዕሴቶች የሚገለጽበት ከመሆኑም በላይ ለኢኮኖሚያዊ  እድገት መሰረት የሚሆንበት አቅም እንዳለው ጠቅሰዋል። 

ወጣቶች የባህሉን  ታሪካዊ ዳራ ጠብቀው እንዲያከብሩና ምሁራንም  በጥናታዊ ስራዎች በማገዝና በመሰነድ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የክልሉ መንግስት የባህል ሀብቶችን በማጥናትና በማስተዋወቅ ለትውልድ እንዲሸጋገሩና የቱሪዝም ስበት ማእከል ለማድረግ  መሰራቱንም  አስታውቀዋል።


 

የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ በበኩላቸዉ፣ የ"ማሽቃሮ" ባህላዊ  እሴቶች ጎልተው እንዲወጡ በቅንጅት   እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዓሉ ከትዉልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገርና በማይዳሰስ ቅርስነት በዩኒስኮ እንዲመዘገብ የተጀመረዉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።


 

የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻዉ ከበደ  እንደገለፁት፣ የ"ማሽቃሮ" የዘመን መለወጫ በይቅርታና በተስፋ  ወደ አዲስ አመት የሚሻገሩበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዓሉ በእርሻና አከባቢ ጥበቃ እንዲሁም  በሰላምና በሌሎች ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት የሚገመገሙበት እንዲሁም የሰራ የሚሸለምበትና ደካማው የሚወቀስበት በመሆኑ የስራ ባህልን የሚያበረታታ ነው ብለዋል ። 

በበዓሉ ላይ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ነዋሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም