የግብጽ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ቦታ የሌለው ኋላቀር አካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የግብጽ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ቦታ የሌለው ኋላቀር አካሄድ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ)፦ የግብጽ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ እና የውሃ የበላይነት ህልም በ21ኛው ክፍለ ዘመን ፈጽሞ ቦታ የሌለውና ኋላቀር አካሄድ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ኢትዮጵያ ዓባይን ጨምሮ ያሏትን የተፈጥሮ ሀብቶቿን የማልማት እና የቀጣዩን ትውልድ ፍላጎት የማሟላት ሉዓላዊ መብቷን በአግባቡ እንደምትጠቀምም ሚኒስቴሩ አስገንዝቧል።
ኢትዮጵያ ዓባይን ጨምሮ ያሏትን የተፈጥሮ ሀብቶቿን የማልማት ሉዓላዊ መብቷ የተጠበቀ መሆኑንም አመልክቷል።
በቅርቡ የግብፅ የውሃ ሀብትና መስኖ ሚኒስትር ኢትዮጵያውያንን በመዝለፍ የሰጡት አስተያየት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና ግብጽ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ባላት ግንኙነት የምትከተለውን የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ በግልጽ ያሳየ መሆኑን አመልክቷል።
ግብጽ ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት የውሃ ሀብታቸውን የሚጠቀሙት እሷን ጠይቀውና ፈቃድ አግኝተው ብቻ ነው ብላ ማመኗ ሁልጊዜም የበላይ ልሁን ከሚለው ኋላ ቀር እሳቤዋ የሚመነጭ መሆኑን ገልጿል።
ይህ የግብጽ አቋም ከእውነት የራቀ እና ፍጹም አስመሳይነት የተሞላበት መሆኑን ሚኒስቴሩ ጠቁሟል።
ግብፅ ከዚህ ቀደም የትኛውንም የተፋሰሱ ሀገራት ፈቃድ ሳትጠይቅ የአስዋን ታላቁን ግድብ መገንባቷን መግለጫው አውስቷል።
የግብፅ ባለሥልጣናት የሚያሰሙት ጥላቻ የሞላበት ንግግር እና የሚከተሉት አሻሚ አካሄድ፤ በተፋሰስ ሀገራት መካከል ሊኖር ከሚገባው የትብብር መንፈስ ጋር ፈጽሞ የሚቃረን መሆኑ ተመላክቷል።
ኢትዮጵያ ዓባይን ጨምሮ ያሏትን የተፈጥሮ ሀብቶቿን የማልማት እና የቀጣዩን ትውልድ ፍላጎት የማሟላት ሉዓላዊ መብቷ የተጠበቀ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስገንዝቧል።
ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የአለመግባባትና የንትርክ ምንጭ ሳይሆን ትብብርን፣ የጋራ እድገትንና የቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ መሆን እንዳለባቸው በጽኑ ታምናለች ብሏል ሚኒስቴሩ በመግለጫው።
አንዱ አካል ብቻ ተጠቃሚ የሚሆንበት እና የተፋሰሱ ሀገራትን መብት ነፍጎ የበላይነትን በጉልበት ለመጫን የሚደረግ ጊዜ ያለፈበት አካሄድ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ሲል ሚኒስቴሩ አስገንዝቧል።
አንዳንድ አካላት የዓባይን ወንዝ እንደ ጸጥታና ግጭት አጀንዳ ብቻ ማየትን ሲመርጡ፣ ኢትዮጵያ ግን የተፋሰሱን የረጅም ጊዜ ደህንነትና ዘላቂነት ለማረጋገጥ ሰፊ ተግባራትን ማከናወኗን ገልጿል።
ኢትዮጵያ በውሃ ተፋሰስ አካባቢዎች የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ማድረጓን፣ ሰፊ የችግኝ ተከላና የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ማከናወኗን እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን በዘላቂነት እየሰራች እንደሚገኝ ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አዎንታዊ እርምጃ ከግብጽ ጠላትነት ከሞላበት የተሳሳተ ትርክት አንጻር ሲታይ ፍጹም የተለየ እና የሰለጠነ አካሄድ መሆኑን አመልክቷል።
በመሆኑም ግብጽ ጊዜው ካለፈበት ፖሊሲ ወጥታ፣ ጉዳዩን በጋራ መከባበርና የሁሉንም ወገኖች የረጅም ጊዜ ጥቅም በሚያከብር የ21ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ ልትመለከተው ይገባል ብሏል።
ግብጽ አሮጌና ጊዜ ያለፈባቸውን የበላይነት ህልሞች በመተው፣ አዲሱን የትብብር እውነታ መቀበል የሚገባበት ጊዜ አሁን መሆኑን ሚኒስቴሩ አሳስቧል።