ቀጥታ፡

 የ"ዮ-ማስቃላ" በዓል እሴቶች ለሕዝቦች አብሮ መኖር፣ ለዘላቂ ሰላምና ልማት ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ ነው

አርባ ምንጭ፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ)፦የጋሞ ዘመን መለወጫ በዓል "ዮ-ማስቃላ" በዓል እሴቶች ለሕዝቦች አብሮ መኖር፣ ለዘላቂ ሰላምና ልማት ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ተናገሩ።

የጋሞ የዘመን መለወጫ በዓል "ዮ ማስቃላ" በአርባ ምንጭ ከተማ ዓለም አቀፍ ስታዲየም በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ ይገኛል።


 

በወቅቱም ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እንደገለፁት፤ የ"ዮ-ማስቃላ" በዓል እሴቶች ለሕዝቦች አብሮ መኖር፣ ለዘላቂ ሰላምና ልማት ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።

እንዲሁም "ዮ ማስቃላ" የሰላም፣ የአንድነት፣ የመቻቻል እና የብልጽግና ተምሳሌት የሆነ የሕዝብ የጋራ ሀብት ነው ብለዋል።

የጋሞ የዘመን መለወጫ በዓል የታፈረች፣ የበለጸገችና የተከበረች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት እንዲሳካ ብሎም ለክልሉ ሰላም፣ መቻቻልና ብልጽግና ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።


 

"ዮ ማስቃላ"ን ጨምሮ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ እሴቶች ለሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና ለቱሪዝም ልማት አስተዋጽኦ በማበርከት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እንዲያሳድጉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በዓሉ የታፈረች፣ የበለጸገችና የተከበረች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት እንዲሳካ ጉልህ ሚና እንደሚጫወትም አመልክተዋል።

የክልሉ መንግሥት "ዮ ማስቃላ"ን የመሰሉ የሰላም፣ የመቻቻል፣ የአብሮነት፣ የአንድነትና የይቅርታ እሴቶችን በማጠናከር ለክልሉ ብሎም ለሀገር ገጽታና ኢኮኖሚ ግንባታ እንዲውሉ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።


 

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ (ዶ/ር) "ዮ ማስቃላ" በዓል የደስታ፣ የምስጋናና የአንድነት ብሎም ወደ ሰላም፣ ፍቅርና ዕድገት የመሻገር ምልክት መሆኑን ተናግረዋል።

በዓሉ የሕዝቡ የሸማ ጥበብና የምግብ አዘገጃጀት ሥርዓት የሚንጸባረቅበት ብሎም ሕዝቡን አንድ የሚያደርጉ የጋራ እሴቶች ጎልተው የሚወጡበት መሆኑንም ገልጸዋል።

የአካባቢውን መልካም እሴቶች ጠብቆ በማቆየት ለትውልድ ለማስተላለፍ የዞኑ አስተዳደር የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።

''ዮ-ማስቃላ'' የጋሞዎችን የአብሮነት፣ የሰላምና የፍትሕ እሴቶች አቅፎ የያዘ የሕዝብ የጋራ ሀብት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መስፍን መንዛ (ዶ/ር) ናቸው።


 

በዓሉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አንድምታ አለው ያሉት ከንቲባው፣ ለሀገር አንድነትና ጽናት የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል።

የሕዝቡን አንድነት በማጠናከር የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን በማሳካት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የከተማ አስተዳደሩ አበክሮ እንደሚሠራም ጠቁመዋል።

በበዓሉ ላይ የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞን፣ የከተማ አስተዳደርና የወረዳ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የተጋበዙ ተወካዮችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም