ነገን የዋጀ የኢትዮጵያ ጉዞ - ኢዜአ አማርኛ
ነገን የዋጀ የኢትዮጵያ ጉዞ
ኢትዮጵያ የዛሬን ተፎካካሪነት ብቻ ሳይሆን የነገውን ዓለም አሻግራ በመመልከት፣ አርቆ አሳቢነት በተሞላበት መንገድ የዲጂታል ምህዳሯን በጽኑ መሠረት ላይ እየገነባች ትገኛለች።
ይህ "ነገን የዋጀ የልማት ጉዞ" በቃላት ሳይሆን በተጨባጭ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችና በዕውቀት በተደገፉ የቴክኖሎጂ እርምጃዎች እየተረጋገጠ ይገኛል።
ወጣቶችን በኮዲንግ፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና በዲጂታል ክህሎት ማበቃት የነገዋን ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ማዕከል የማድረግ ትልቅ ራዕይ መገለጫ ነው።
የ"5 ሚሊዮን ኮደርስ" ኢኒሼቲቭ በአሁኑ ወቅት ከታቀደው በላይ ተሳክቶ ወደ 7 ሚሊዮን ኮደርስ ማደጉ የወደፊቷን ሀገር በሰው ሀብት የመታደግ አርቆ አሳቢነት ማሳያ ነው። ይህም ነገ የአፍሪካን የዲጂታል ገበያ በበላይነት የሚቆጣጠሩ አቅም ያላቸው ወጣቶችን የማፍራቱን ስራ በጽኑ መሰረት ላይ እያስቀመጠው ነው።
ለዲጂታል ትስስርና ለገበያ ተሳትፎ ዋነኛ መሠረት የሆነው የቴሌኮም ተመዝጋቢ ደንበኞች ቁጥር ሀገራዊ ለውጡ ሲጀመር ከነበረበት ከ37 ነጥብ 9 ሚሊዮን ወደ 85 ሚሊዮን በላይ ማደጉ፣ የኢትዮጵያውያንን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት አዲስ ደረጃ ላይ አሸጋግሮታል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ50 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የተመዘገቡ ሲሆን፤ ይህም የገበያ ምዝገባ እና የማረጋገጫ ወጪዎችን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ ለአገልግሎቶችና ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ትልቅ ምቾትና እምነት ፈጥሯል።
እንደ "መሶብ" ያሉ የዲጂታል አገልግሎት መስጫ ተቋማት በአጭር ጊዜ ውሰጥ በሁሉም የኢትዮጵያ ከባቢዎች እየሰፉ ሲሆን፤ ዲጂታል ግብይትም በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ትልቁን ስፍራ እየያዘ ይገኛል።
ይህ አሰራር አገልግሎትን ለማቀላጠፍ ከማስቻሉ ባሻገር፣ ጥሬ ገንዘብ ለማተም እየወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ እያስቀረ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት ዓመታዊ የዲጂታል ግብይት መጠን 24 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር መድረሱ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታው ስኬታማነት ማረጋገጫ ነው።
መደመር ያለፉ እውቀቶችን፣ የዛሬ አቅሞችንና የነገ ተስፋዎችን አዋህዶ ሀገርን የማነፅ ፍልስፍና ነው። በቴክኖሎጂው ዘርፍ የሚከናወኑት እነዚህ የሰው ሀብት ልማት፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ የፋይዳ መታወቂያና የዲጂታል ግብይት ስኬቶች በሙሉ "በመደመር" መርህ የወጣቶችን እውቀትና ሀገራዊ አቅምን ለመገንባት የተለሙ ናቸው።
ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ እያከናወነች ያለችው ሥራ የዛሬ ፍላጎቶችን የመመለስ ያህል፣ ነገ የሚገጥማታን ዓለም አሻግራ የመመልከትና ለዲጂታሉ ዘመን ተወዳዳሪ ሆኖ የመቅረብ ጥበብ ነው። ይህ ጉዞ ነገን ዛሬ የመገንባት፣ የትውልድን ተስፋ የማረጋገጥና የኢትዮጵያን ብልፅግና የማስቀጠል የጋራ ስኬታችን ማሳያም ጭምር ነው።