የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የፍትሐዊ ተጠቃሚነትና የሉዓላዊነት መሠረት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የፍትሐዊ ተጠቃሚነትና የሉዓላዊነት መሠረት ነው
መቱ ፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ቀጣናዊ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ እና የሀገሪቱን ታሪካዊና ዘላቂ ሉዓላዊነት ያማከለ መሠረታዊ ጥያቄ መሆኑን የመቱ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
ምሁራኑ የባሕር በር ጥያቄው ምላሽ ማግኘት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሉዑላዊነት ከመጠበቅ ባሻገር፣ የቀይ ባሕርና የቀጣናው አገራት በጋራና በፍትሐዊነት የሚበለፅጉበትን መንገድ የሚያመቻች መሆኑን አስረድተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የታሪክ መምህር ወንዳቸው ምትኩ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ አስፈላጊ ከመሆኑ ባሻገር የሀገሪቱን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሠረታዊ አጀንዳ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነቷን ያጣችው ግልጽነት በጎደለውና የሕዝብ ውሳኔ ባልተካተተበት ሁኔታ መሆኑን ያስታወሱት ምሁሩ፤ አሁን የሚቀርበው የባሕር በር ጥያቄ ትክክለኛና በማንም አጎራባች ሀገር ላይ ጉዳት የማያደርስ ህጋዊ የመብት ጥያቄ መሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ስኬታማ ለማድረግ የኢኮኖሚ፣ የቴክኖሎጂ እና የዲፕሎማሲ አቅሟን በከፍተኛ ደረጃ ማጠናከር እንደሚገባት መክረዋል።
የራሷ የባሕር ወደብ የሌላት ሀገር ለዘርፈ ብዙ ችግሮች እንደምትጋለጥ ያብራሩት ዶክተር ወንዳቸው፤ ይህ ሁኔታ በሀገሪቱ የገቢና ወጪ ንግድ እንዲሁም በአጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው የሕዝብና ውጭ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ረዳት ፕሮፌሰር ተገኝ ደምሴ በበኩላቸው፤ የባሕር በር ለአንድ ሀገር የጀርባ አጥንት መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የራሷን ወደብ ለመመለስ የምታደርገው ጥረትም ለጠንካራ ኢኮኖሚ፣ ለፖለቲካዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነት እና ለሀገራዊ ሉዓላዊነት መረጋገጥ አስፈላጊና ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በሕገ-ወጥ መንገድና የሕዝብ ይሁንታ ባልተቸረው ሁኔታ ያጣችውን የባሕር በር ለማስመለስ በሕጋዊ መንገድ የምታደርገው ጥረትና የምታቀርበው ጥያቄ ተገቢና ወሳኝ መሆኑን ረዳት ፕሮፌሰር ተገኝ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የሌሎችን ሀገራት ወደብ በመጠቀሟ ምክንያት ለወደብ አገልግሎት የምታወጣው ከፍተኛ ወጪ የኑሮ ውድነትን ከመፍጠር በላይ፣ የገቢና ወጪ ንግዷ ግልጽ መሆን ሀገራዊ ሚስጥሯን ለመጠበቅ ከፍተኛ ስጋት ደቅኖባታል ብለዋል።
በተጨማሪም የቀጥተኛ የባሕር በር አለመኖር ሀገሪቱን በባሕር ለሚፈጸሙ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና የባሕር ላይ ውንብድናዎች ተጋላጭ በማድረግ፣ ለተደራራቢ የጸጥታ ስጋቶች በር የሚከፍትባት መሆኑን ምሁራኑ አስረድተዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት ከሀገሪቱ ሉዓላዊነት ጋር በቀጥታ የተያያዘ በመሆኑ፣ ጥያቄው ምላሽ እስኪያገኝ መላው ሕዝብ በጋራ መስራት እንዳለበት በአጽንኦት አመላክተዋል።