ቀጥታ፡

እምቅ የቱሪዝም ሀብቶችን ለማልማት የተጀመሩ ስራዎች አበረታች ውጤት አስመዝግበዋል 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ያሉ እምቅ የቱሪዝም ሀብቶችን በማልማት ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች አበረታች ውጤት ማስመዝገባቸውን የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ነጋ ወዳጆ ገለፁ።

የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን 6ኛውን የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት አከባበር አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።

ምክትል ኮሚሽነሩ በሰጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች የበለፀገ የተፈጥሮ፣ የባህልና የቱሪስት መስህቦች ያሏት ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በክልሉ ያሉ እምቅ የቱሪዝም ሀብቶችን ለማስተዋወቅ፣ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ጋር በዘርፉ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እና የገበያ ትስስርን ለማጠናከር በማሰብ የቱሪዝም ሳምንቱ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

በዚሁ መሰረት 6ኛው የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት ከመስከረም 19 እስከ 21 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሄድ ጠቁመው፤ በመርሀ ግብሩም ከ20 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ከ100 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ኤግዚቢተሮች እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል።

የቱሪዝም ሳምንቱ በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር በመግለፅ፤ ከእነዚህም መካከል የባህል፣ የኪነ-ጥበብ እና የቱሪዝም ሀብቶችን ማስተዋወቅ፣ ከተለያዩ ተሳታፊዎች ጋር ልምድ ልውውጥ ማድረግ እና በዘርፉ ላይ ትኩረት ያደረገ የፓናል ውይይት ማካሄድ ተጠቃሽ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ሁነቱ መዘጋጀቱ የክልሉን እና የሀገሪቱን የቱሪዝም ሀብቶች እንዲሁም የኢንቨስትመንት አማራጮች ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም