መስቀል እና ኢሬቻ የኢትዮጵያን እሴቶች ለዓለም በሰፊው የሚያስተዋውቁ በዓላት ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
መስቀል እና ኢሬቻ የኢትዮጵያን እሴቶች ለዓለም በሰፊው የሚያስተዋውቁ በዓላት ናቸው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ)፦የመስቀል እና ኢሬቻ በዓላት የኢትዮጵያን የሰላም፣ የፍቅር እና የአብሮነት እሴቶች ለዓለም በሰፊው የሚያስተዋውቁ ድንቅ በዓላት መሆናቸውን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።
በኢትዮጵያ በመስከረም ወር በድምቀት የሚከበሩት የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላት ታላቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ከፍታ ያላቸው ሀገራዊ እሴቶች ናቸው።
በዓላቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሀገር ውስጥ ዜጎች እና ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች በአደባባይ የሚሳተፉባቸው ሲሆን፣ ሁነቶቹ ማህበራዊ ትስስርን ለማጠናከር እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ይበልጥ ለማላቅ እጅግ ወሳኝ ሚና አላቸው።
የኢትዮጵያን የሰላም፣ የፍቅር እና የአብሮነት እሴቶች ለዓለም ህብረተሰብ በሰፊው የሚያስተዋውቁ ድንቅ መድረኮችም ናቸው።
እነዚህ ግዙፍ ሀገራዊ እሴቶች የኢትዮጵያን ማህበራዊ ሀብትና የቱሪዝም አቅም በአንድ ላይ የሚያሳዩ የኩራት ምንጮች ናቸው።
በዓላቱ የኢትዮጵያ ህብረ-ቀለም ባህልና ማህበራዊ መስተጋብር በይበልጥ ጎልቶ እንዲታይም ያደርጋሉ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት፣ የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላት የህዝብን አንድነት ከመጠበቅ፣ ማህበራዊ መስተጋብርን ከማጠናከር እንዲሁም የኢኮኖሚ እና የቱሪዝም እንቅስቃሴን ከማሳደግ አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።
አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል አቶ መገርሳ ታዎኦቶ እንደገለጹት፣ በዓላቱ በሰፊው የሚከበሩ በመሆናቸው የህዝብን አንድነት፣ መተሳሰብ እንዲሁም ሀገራዊ ፍቅርን በማጎልበት ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ።
እነዚህ ዓላት አብሮነትን ከማጽናት ባለፈ በቱሪዝም ረገድ ለሀገር ዕድገት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።
አቶ ተስፋዬ ግርማ በበኩላቸው፣ በዓላቱ ህዝቡ አብሮ ማዕድ የሚቋደስበት እና ባህላዊ እና ሀይማኖታዊ እሴቶቹን የሚያንጸባርቅበት በመሆኑ ማህበራዊ ትስስርን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።
በተለይም መልካም ገጽታን በመገንባት እና የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን በመሳብ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስገኙም አክለዋል።
ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ዜጎች በበዓላቱ ላይ መገኘት የየአካባቢውን ባህል እና ስርዓት እንዲካፈሉ ዕድል በመፍጠር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን እንደሚያጎለብት የተናገሩት ደግሞ አቶ በለጠ ስዩም ናቸው።
በበዓላቱ ወቅት የባህል አልባሳት፣ የሆቴል እና ሬስቶራንት አገልግሎቶች እንዲሁም የባዛር እና የሲምፖዚየም ዝግጅቶች በመስፋፋታቸው ለወጣቶች ሰፊ የሥራ እድል እንደሚፈጥሩም አብራርተዋል።
አቶ ጉደታ ኢካ እና ወይዘሮ ብርቱካን ስዩም በበኩላቸው፣ የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላት በኢትዮጵያዊ ጥበብ የሚመረቱ አልባሳት በሰፊው የሚቀርቡበት ትልቅ አጋጣሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።