በደቡብ ወሎ ዞን የምርጥ ዘር ፍላጎትን በራስ አቅም ለመሸፈን የሚደረገው ጥረት ውጤታማ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ወሎ ዞን የምርጥ ዘር ፍላጎትን በራስ አቅም ለመሸፈን የሚደረገው ጥረት ውጤታማ ነው
ደሴ ፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ወሎ ዞን የአርሶ አደሩን የምርጥ ዘር ፍላጎት በራስ አቅም ለመሸፈን የሚደረገው ጥረት ውጤታማ መሆኑን
የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ይመር ሰይድ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዞኑ በ533 ሄክታር መሬት ላይ ምርጥ ዘር በማባዛት በራስ አቅም ፍላጎቱን ለማሟላት እየተሰራ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት እየተባዛ ያለው የስንዴ፣ የጤፍ፣ የማሽላና የባቄላ ምርጥ ዘር ሰብል በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ መሆኑን ነው የጠቀሱት።
ምርጥ ዘሩን ማባዛት የተቻለውም አርሶ አደሮችን፣ ባለሃብቶችንና ሌሎች አጋር አካላትን በማሳተፍ መሆኑን አስረድተዋል።
በምርጥ ዘር ማባዛት ስራ ላይ የተሰማሩ አካላትን በመደገፍ ለሰብሉ አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረግ በመቻሉ ከ15 ሺህ 500 ኩንታል በላይ የምርጥ ዘር ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
ይህም ጥራት ያለውና በበቂ መጠን ዘር በማምረት ለአርሶ አደሮች በወቅቱ ለማቅረብና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ ለማሳካት እንደሚያስችል ነው የተናገሩት።
በዞኑ በወረኢሉ ወረዳ የ03 ቀበሌ አርሶ አደር ተስፋዬ ጋሻው በበኩላቸው፣ አንድ ሄክታር መሬታቸው ላይ የስንዴ ምርጥ ዘር እያባዙ መሆኑን ተናግረዋል።
በባለሙያዎች እገዛ ሰብሉን ከአረምና ተባይ መከላከል መቻላቸውን ጠቁመው ከ50 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
ግማሽ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ የባቄላ ምርጥ ዘር እያባዙ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በለጋምቦ ወረዳ የ04 ቀበሌ አርሶ አደር ሰይድ መሀመድ ናቸው።
ከዚህም ለአካባቢው አርሶ አደር የተሻለ የምርጥ ዘር ለማቅረብ በግብርና ባለሙያዎች ታግዘው እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን በመኸሩ ወቅት አጠቃላይ በተለያየ የሰብል ዘር ከለማው 432 ሺህ ሄክታር መሬት ከ15 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።