ቀጥታ፡

ከጨበራ እስከ ጎርጎራ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ)፦ከጨበራ እስከ ጎርጎራ 

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ጸጋዎች እንዲሁም በታሪክ፣ በባህል እና በታሪካዊ ቅርሶች የታደለች ሀገር መሆኗ ይታወቃል። ይሁን እንጂ እነዚህ እምቅ ሃብቶች ለበርካታ ዓመታት ተገቢውን ትኩረት ሳያገኙ፣ ሳይለሙና የሀብት ምንጭ ሳይሆኑ ተዘንግተው መቆየታቸው የሚታወቅ ነው።

የመደመር መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ በሰጠው ትኩረት ዘርፉ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ከተካተቱ አምስት ሴክተሮች አንዱ ሆኖ መተግበር ጀምሯል። በዚህም በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማሻሻልና አዳዲስ መዳረሻዎችን የማልማት ስራ በስፋት ተከናውኗል፤ እየተከናወነም ይገኛል። 

በዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጭነት በጥቂት ዓመታት ውስጥ የተከናወኑ የ"ገበታ ለሸገር"፣ "ገበታ ለሀገር" እና "ገበታ ለትውልድ" የልማት መርሃ-ግብሮች የቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ እመርታና ማንሰራራት አምጥተዋል። በእነዚህ ኢንሸቲቮች ተደብቀው የቆዩና በሁሉም ማእዘናት የነበሩ  መሠረተ ልማቶችን በማልማት ጥቅም ላይ ማዋል ተችሏል።


 

ለኢትዮጵያ ተፈጥሮ የለገሳትን ውብ መልክዓ ምድሮች፣ ሀይቆች፣ ብሔራዊ ፓርኮች እና ታሪካዊ ስፍራዎች ይበልጥ በማልማት የዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ ቱሪዝም መዳረሻነቷን ከፍ አድርጓል።

የቱሪዝም ልማቱ ሀገርን እና ትውልድን መሰረት አድርጎ በሁሉም አካባቢዎች በርካታ ግንባታዎችን እውን አድርጓል። ከቀድሞው የተገደበ የቱሪስት እንቅስቃሴ ወጥቶ፣ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችንና ሪዞርቶችን በመገንባት ረገድ አስደናቂ ስራዎች ተከናውነዋል።

በጣና ሐይቅ ዳርቻ ላይ የተገነባው የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ለቱሪስቶች ምቾትና ለሐይቁ ውበት ግርማ ሞገስ ሆኖ የተገነባ ነው። የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ጋር ተሰናስሎ የተገነባው  ሎጅም የተፈጥሮን ውበት ከዘመናዊ የቅንጦት አገልግሎት ጋር ያሰናሰለ አስደናቂ ስፍራ መሆኑ ይታወቃል። የ«ገበታ ለትውልድ» ሁለተኛ ምዕራፍ ማሳያ የሆነው ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ደግሞ የወሎን ማህበራዊ መስተጋብር እና የአብሮነት እሴት የሚያጎለብት፣ ለአይን ማራኪ እና ዘመናዊ መዝናኛ ሆኖ የታነጸ ነው።


 

በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብተው ትኩረት ከሰበሰቡ አዳዲስ የቱሪዝም እና የልማት መዳረሻዎች መካከል ቤኑና መንደር አንዱ ነው። የ«ይቻላል» እምነት ቋሚ ምስክር ተብሎ የሚታወቀው ይህ አካባቢ፣ አካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ስበት በመጠቀም የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶችን ትኩረት የሳበ ውብ መናኸሪያ ሆኗል።

በእሳተ ገሞራ ፍንዳታ የተፈጠረው እና ውብ ውበቱን የያዘው የወንጪ ሐይቅ፣ ዛሬ ላይ ከማህበረሰቡ ጋር በተቀናጀ መልኩ በለማው ኢኮ-ሎጅ ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ያገኘ መዳረሻ መሆኑ ይታወቃል። በሶማሌ ክልል ከጅግጅጋ ከተማ በ385 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባው ታላቁ የሸበሌ ሪዞርትም የክልሉን የቱሪዝም ልማት በእጅጉ ያነቃቃ ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑ ይታወቃል። 

የዳናክል በረሃ እና ኤርታአሌ ያሉ ድንቅ የተፈጥሮ ጸጋዎችን የያዘው የአፋር ክልል ቱሪዝምን ለማነቃቃትና የጎብኚዎችን ቆይታ ለማራዘም "ከፈንታሌ እስከ ኤርታአሌ" የተሰኘ የቱሪዝም ልማት ፕሮጀክት ጨምሮ ዘመናዊ ሪዞርቶችና መዳረሻዎች እንዲስፋፉ ተደርጓል። 


 

በድምሩ ከጨበራ እስከ ጎርጎራ፣ ቤኑና፣ ወንጪ፣ ሎጎ ሃይቅ እንዲሁም የሀሮ ደንዲ ሎጅ የሀገሪቱን ገጽታ የቀየሩና የቱሪዝም ዘርፉን እድገትና ማንሰራራት እውን ካደረጉት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። የህዳሴ ግድብም ከሃይል ልማት ባለፈ አይነተኛ የቱሪዝም መሰህብ ስፍራ ሆኖ የንጋት ሃይቅ ዓሳ የሚመረትበትና ቱሪስቶች የሚስተናገዱበት ተመራጭ ስፍራ ሆኗል።

በመደመር መንግስት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ከመገንባት ባለፈ የቆዩትን የማደስና ቅርሶችን የመጠበቅ እንዲሁም የመንከባከብ ስራ በስፋት ተከናውኗል። በሁሉም ክልሎች እምቅ ሃብቶችን በመለየት የማልማትና የነበሩትን የመጠበቅ ስራ ተሰርቷል።

ለትውልድ የሚሻገር የቅርስ ጥበቃና መዳረሻዎችን የማልማት ተግባር የኢትዮጵያን ብዝሃ-ሃብት በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። በአጠቃላይ ባለፉት አምስት ዓመታት የተከናወኑ የልማት ኢኒሼቲቮች በተለይም በቱሪዝም ሴክተር መሰረታዊ ለውጥና ስኬት ማስመዝገብ የቻሉ ተጨባጭ ውጤቶችም ያመጡ መሆናቸውን መናገር ይቻላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም