ቀጥታ፡

በጅማ ዞን በቅንጅት በተካሄደ የዘር ማባዛት ሥራ የበቆሎ ምርጥ ዘር እጥረትን መቅረፍ ተችሏል

ጅማ ፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ)፦በጅማ ዞን የኅብረት ሥራ ዩኒየኖችና አርሶ አደሮች በጥምረት ባካሄዱት የዘር ማባዛት ሥራ የበቆሎ ምርጥ ዘር እጥረትን መቅረፍ  መቻሉ ተገለጸ፡፡

በጅማ ዞን የበቆሎ ምርታማነትን ለማሳደግና የአካባቢውን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያስችል ጥራት ያለውና በወቅቱ የሚቀርብ የበቆሎ ምርጥ ዘር እጥረት ዋና ማነቆ ሆኖ ቆይቷል። 

ቀደም ሲል አርሶ አደሩ የሚፈልገውን ያህል ምርጥ ዘር ማግኘት ባለመቻሉ፣ ወይም አቅርቦቱ በወቅቱ ባለመድረሱ ምክንያት ምርታማነታቸው ዝቅተኛ የሆኑ ዘሮችን ለመጠቀም ይገደድ ነበር።

ይህንን ዘላቂ ችግር ለመፍታት የጅማ ዞን የኅብረት ሥራ ኤጀንሲ፣ የኅብረት ሥራ ዩኒየኖችና አርሶ አደሮች በጥምረት በመንቀሳቀስ በአካባቢው ላይ ያተኮረ የዘር ማባዛት ፕሮግራም ዘርግተዋል። 

አርሶ አደሮችም በቡድንና በኅብረት ሥራ ማህበራት ተደራጅተው፣ አስፈላጊውን የቴክኒክና የግብዓት ድጋፍ እያገኙ የምርጥ ዘር ብዜት ሥራው አካል እንዲሆኑ ተደርጓል። 

ይህ የተቀናጀ አሠራር የውጭ አቅርቦት ጥገኝነትን በማስቀረት በአካባቢው የሚመረተው ምርጥ ዘር ለዞኑ አርሶ አደሮች በበቂ ሁኔታና በወቅቱ እንዲደርስ አስችሏል።


 

የዞኑ የህብረት ሥራ ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ድማሙ ንጋቱ እንዳሉት፣ በዞኑ ቀደም ሲል የበቆሎ ምርጥ ዘር አቅርቦት ከፍላጎቱ ጋር የማይመጣጠን በመሆኑ እጥረት ነበር።

ይህንን ችግር ለመፍታት የዞኑን የህብረት ሥራ ዩኒየኖች በማሳተፍ በተለያዩ ወረዳዎች በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ በኮንትራት እርሻ የዘር ማባዛት ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።

በዞኑ የበቆሎ ምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል ያሉት ሃላፊው፤ ከዞኑ የዘር ፍላጎት በላይ ማምረት በመቻሉም እንደ ቡኖ በደሌ፣ ኢሉ አባ ቦራና ምዕራብ ሸዋ ላሉ አጎራባች ዞኖች  ዘር እየቀረበ መሆኑን ጠቁመዋል።

የዘር ማባዛት ሥራው የበቆሎ ምርጥ ዘር አቅርቦትን ከማሻሻል ባለፈ የአርሶ አደሮችን ገቢ ለማሳደግ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም አቶ ድማሙ ገልጸዋል።


 

በ2018 ዓ.ም በተለያዩ ወረዳዎች የተባዛውን የበቆሎ BH661 ምርጥ ዘር በመሰብሰብ ብቻ ከ580 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ገቢ ለአርሶ አደሮች ማስገኘት መቻሉን ኃላፊው ጠቅሰዋል።

በዚህ የምርት ዘመንም የሊሙ ኢናሪያና የጅማ ዩኒየኖች በኖኖ በንጃ ወረዳ በድምሩ በ11 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የበቆሎ ምርት እያከናወኑ መሆኑን አቶ ድማሙ ገልጸዋል።

አቶ ድማሙ እንዳብራሩት፣ የዘር ማባዛት ሥራው በበቆሎ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን የስንዴና የአኩሪ አተር ዘርንም ያካትታል። 

በ2019 ዓ.ም ከ1 ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተለያዩ የሰብል ዘሮችን የማባዛት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።


 

የሊሙ ኢናሪያ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ ድሉ ፀጋዬ በበኩላቸው፣ ዩኒየኑ የተመረጠ የበቆሎ ዘር አቅርቦትን ለማሳደግ በዘር ማባዛት ሥራ ላይ መሳተፉን ገልጸዋል።

በዚህ ዓመትም ከ7 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተመረጠ የበቆሎ ዘር በማባዛት ከ20 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየሰራ መሆኑን አቶ ድሉ አስታውቀዋል።

የጅማ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍራ ራያ በበኩላቸው፣ ዩኒየኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተመረጠ የበቆሎ ዘር አቅርቦት ችግርን ለመፍታት በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።


 

በዚህ ዓመትም በ400 ሄክታር መሬት ላይ የተመረጠ የበቆሎ ዘር እያባዛ ሲሆን፣ ከዚህም 13 ሺህ ኩንታል የበቆሎ ዘር ለማግኘት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የጅማ ዞን ሊሙ ኮሳ ወረዳ አርሶ አደር ታጁ ሼህ ጀማል በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም የበቆሎ ምርጥ ዘር በበቂ ሁኔታ አለመገኘቱ በእርሻ ሥራቸው ላይ ችግር ሲፈጥር እንደነበር ተናግረዋል።

ካለፈው ዓመት ጀምሮ ግን በቂ የበቆሎ ምርጥ ዘር በማግኘታቸው ምርታማነታቸውን ማሳደግ መቻላቸውን ነው የገለፁት።


 

ሌላኛው አርሶ አደር ጃፈር አባቡልጉ የቀረበላቸው ምርጥ ዘር፣ ምርታማነትን ከፍ የሚያደርግ እና በሽታን የሚቋቋም መሆኑን ተናግረዋል።

አርሶ አደሮቹ በቀረበላቸው ምርጥ ዘር በመጠቀም ከፍተኛ የበቆሎ ምርት እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም