ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይልን ወደ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ለመቀየር ሁሉን አቀፍ ስራዎችን እያከናወነች ነው- ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2019 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል አቅሟን ወደ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ለመቀየር እየሰራች እንደምትገኝ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።

81ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ከመስከረም 8 ቀን 2019 ዓ.ም አንስቶ በኒው ዮርክ እየተካሄደ ይገኛል።
 
“መተማመንን ዳግም መገንባት እና አዳዲስ ለውጦችን በአግባቡ መምራት፣ ለሁሉም የሚሰራ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን መፍጠር”  የጉባኤው መሪ ሀሳብ ነው።

በፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑካን በጉባኤው ላይ እየተሳተፈ ነው።

ፕሬዝዳንት ታዬ ከጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በተካሄደ የዓለም አቀፍ የታዳሽ ኃይል ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል።

ፕሬዝዳንቱ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የዓለም አቀፍ የታዳሽ ኢነርጂ አጀንዳ ኃይል ማመንጨት ላይ ብቻ ተወስኖ መቅረት እንደሌለበት ገልጸዋል።

ኤሌክትሪክን ወደ እውነተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ለመቀየር የሚያስችሉ የማስተላለፊያ መስመሮችን፣ ቴክኖሎጂዎች  እና የኃይል ማከፋፈያ መሰረተ ልማቶችን በፋይናንስ መደገፍ ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከፍተኛ የታዳሽ ኃይል እምቅ አቅም ያላቸው ሀገራት ያሏቸውን ሃብቶች ወደ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የኢንዱስትሪ ዕድገት እና ሁሉን አካታች ብልጽግና ለመለወጥ ጠንካራ ዓለም አቀፍ ትብብር እንደሚያስፈልጋቸው አስገንዝበዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች፣ ማከማቻዎች እና ጠንካራ ተቋማዊ አቅም ሳይኖር የሚደረግ የኃይል ማመንጨት ብቻውን ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ማምጣት አይችልም ብለዋል።

በመሆኑም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ድጋፉ ከኃይል ማመንጨት ጀምሮ እስከ ማስተላለፊያ፣ ማከፋፈያ፣ ማከማቻ እና የቤት ለቤት የኃይል አቅርቦትን ጭምር ያካተተ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

ለዚህም ስኬት የፋይናንስ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዝዳንቱ፤ ከሀገር ውስጥ ሀብቶች እና ከዓለም አቀፍ አጋሮች (እንደ የዓለም ባንክ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ እና የአውሮፓ ህብረት 'ግሎባል ጌትዌይ' ፕሮጀክት ጋር በመተባበር) ተፈጻሚ ሊሆኑ የሚችሉ ፕሮጀክቶች መዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል። 

በተለይም ለኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እና መሠረተ-ልማቶች  እንዲሁም ለመለዋወጫ ጣቢያዎች ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የገነባችው በራሷ አቅም እና በህዝብ ሰፊ ንቅናቄ መሆኑን በማስታወስ፣ ይህ የሀገር ውስጥ ባለቤትነት እና ቁርጠኝነት ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ ማሳያ ነው ብለዋል።

በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ከራስ አቅም ጎን ለጎን ዘመናዊ የኃይል አውታሮችን ለመዘርጋት የሚያስችላቸውን ሰፊ ኢንቨስትመንቶችን ለማግኘት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ፕሬዚዳንቱ ለኢትዮጵያ የኃይል ዘርፍ ላደረጉት ዓለም አቀፍ ድጋፍ፣ በተለይም የአውሮፓ ህብረት 'RISED' መርሐ ግብር፣ የዓለም ባንክ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ለሀገሪቱ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት መዘመን እና መጠናከር ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንት በጥቂት የበለጸጉ ሀገራት ብቻ ተወስኖ ከቀረ ዓለም አቀፍ  የኢነርጂ ሽግግር ሊሳካ እንደማይችል አስገንዝበዋል።

በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ዋናው ግብ ከኃይል እምቅ አቅም ወደ ኤሌክትሪክ ተደራሽነት፣ ከተደራሽነት ወደ አምራችነት፣ ከዚያም አልፎ ወደ ኢንዱስትሪ ልማት እና የስራ ዕድል ፈጠራ መሸጋገር መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም