ቀጥታ፡

በዜጎቿ እጅ የለመለመች ምድር - ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ ከአስርት ዓመታት በፊት የደን ሽፋኗ በከፍተኛ ሁኔታ ተመናምኖ ነበር። ይህም ሀገሪቷን ለአየር ንብረት ለውጥ እና አካባቢ ጥበቃ ፈተናዎች ዳርጓት ቆይቷል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጭነትና አነሳሽነትም የደን ሽፋንን ወደ ነባር ይዞታው ለመመለስ እና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም ያለመ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በ2011 ዓ.ም ይፋ ተደረገ።

በዚህ የአረንጓዴ አሻራ ማዕቀፍ ውስጥ ኢትዮጵያውያን የመሪያቸውን ፈለግ በመከተል በመላው ሀገሪቱ ችግኞችን በመትከል ግንባር ቀደም ሚናቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ዘጋርዲያን መርሐ ግብሩን አስመልክቶ ባሰፈረው ረጅም ሐተታ አመልክቷል።  

ሃሊማ ከድር ችግኝ መትከል ስትጀምር ብዙ ሰዎች ይጠራጠሯት እና ይሳለቁባት እንደነበር ለዘጋርዲያን ትገልጻለች።

በሙዝ፣ በዘይቱንና በግሬቪሊያ (Grevillea) ዛፎች እንዲሁም በተለያዩ ፍራፍሬዎች በተሸፈነው አትክልት ስፍራ ውስጥ በእንጨት ወንበር ላይ ተቀምጣ ጅማሮዋ ላይ የነበሩ ፈተናዎችን ወደ ኋላ መለስ ብላ ታወሳለች።

ጎረቤቶቼ ተስፋ አስቆርጠውኝ ነበር ትላለች።

ለአንዳንዶች ከንቱ ድካም ይመስላቸው ነበር፤ ነገር ግን ከጊዜ በኋላ ዛፎችን መትከል ለአየር ንብረት መዛባት እና ለምግብ ዋስትና ችግር  መፍትሄ ሆኖ ሲመጣ ማህበረሰቡ እውነታውን በውል እየተረዳው መምጣቱን ገልጻለች።

በኦሮሚያ ክልል በርበሬ ወረዳ የምትገኘው ሃሊማ ከድር (35 ዓመቷ)፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ዛፎችን በመትከል ለሌሎች አርአያ በመሆን የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች ሆና ብቅ ብላለች።

እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሰፊ የደን መራቆት ባለባት ሀገር የሃሊማ ሥራ ቀላል አልነበረም፤ ከፍተኛ የሞራል ድፍረትና ጽናትን ጠይቋል።

አሁን ሁሉም ነገር ተቀይሯል ትላለች ሃሊማ። የተከለቻቸው ዛፎች አድገው አካባቢዋ በአረንጓዴ ሲደምቅ፣ መጀመሪያ ላይ ሊያደናቅፏት የሞከሩት ሰዎች ጭምር ለድካሟና ለቁርጠኝነቷ አድናቆት መስጠት መጀመራቸውን ትናገራለች።

ለሃሊማ የምተክላቸው ችግኞች ከዛፍነት የዘለለ ትርጉም አላቸው ፣እንደ ቅርብ ጓደኞቿ እና በዓለም ላይ ለአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ተጋላጭነት ካላቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው ማህበረሰቧ ውስጥ ለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች መፍትሄ አድርጋ ትመለከታቸዋለች።

የ«ዘ ጋርዲያን» ጽሑፍ እንደሚያመለክተው፤ በግብርና መስፋፋት፣ በማገዶ እንጨት ፍለጋ እና በከሰል  አጠቃቀም የተነሳ ኢትዮጵያ እጅግ ብዙ ሄክታር መሬት ላይ የነበረ የደን ሽፋኗን አጥታለች።

ይህ ሁኔታ በብዝሃ ሕይወት፣ በአፈር ለምነት እና በውሃ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ከአየር ንብረት ጋር ተያያዥነት ያላቸው አደጋዎች እንዲባበሱ አድርጓል።

የኢትዮጵያ መንግሥት መተግበር ከጀመራቸው በርካታ ኢኒሼቲቮች አንዱ የሆነው ግዙፉ አረንጓዴ አሻራ  የደን ጭፍጨፋ በመቀነስ ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።

በዚህ መርሃ ግብር አማካኝነት የአሁኑን ሳይጨምር ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ 48 ቢሊዮን ዛፎች መተከላቸውን ዘገባው ያመለክታል።

የሃሊማ ጎረቤት ፋጤ አብዱላሂ፣ የሃሊማን ስኬት ከተመለከተች በኋላ በአካባቢ ጥበቃ መሳተፍ ጀምራለች።

ስህተት እንደነበርን አሳይታለች፤ ችግሮች በሀገር በቀል መፍትሄዎች መፈታት እንደሚችሉ በማሳየት አርአያ ሆናለች ስትል ሃሊማን አድንቃለች።  

የኦሮሞ ማህበረሰብ ተፈጥሮዓዊ የወላጅነትና የልጅነት የሥጋ ዝምድና ሳይኖር ከሌላ ሰው አብራክ የተወለደን ልጅ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ ጥቅሙን ጠብቆ እንደ አብራክ ክፋይ ልጅ የማሳደግ (ጉዲፈቻ) ባህል ያለው ነው።

ይሄ እሴት ሃሊማ ለዛፎች በምታደርገው እንክብካቤ ስኬታማ እንድሆን አስችሎኛል ትላለች።

ከችግኞቿ ጋር ያላትን ቁርኝት ከእናትነት ስሜት ጋርም አስተሳስረዋለች። በባህላችን ልጅ በጉዲፈቻ እንደምንቀበለው ሁሉ፣ እኔም እነሱን እንደ ገዛ ልጆቼ አድርጌ ነው የማያቸው ስትል ተናግራለች።

ከባድ የውሃ እጥረት ባለበት አካባቢ የምትኖረው ሃሊማ፤ ችግኞቿን በትጋት ለመንከባከብ እና ለዛፎቹ የሚያስፈልገውን ውሃ ከሌላ ስፍራ ለማምጣት አንድ ሰዓት ገደማ በእግር ትጓዛለች።

የሃሊማ የ13 ዓመት ልጅ አንዋር ሀሰን በእናቱ እንደሚኮራ ገልጾ፣ የእናቱን ፈለግ የመከተል ፍላጎት እንዳለው ይናገራል።

የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚደረገው ትግል ውስጥ የዕድሜ ልክ ቃልኪዳን መግባት እፈልጋለሁ ሲልም ገልጿል።

በአቅራቢያ በሚገኙ ቀበሌዎች የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ አባወራዎችና እማወራዎችም የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩን ተቀላቅለዋል።

ተመናምኖ የነበረው መሬት ወደ ለም አረንጓዴ መልክዓ ምድር እየተለወጠ ይገኛል።

እንደ አካባቢ ጥበቃ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች  ገለጻ ከሆነ፤ ለቤተሰቦችና ለተለያዩ ተቋማት የተሰራጩት በርካታ ሀገር በቀል የችግኝ ዝርያዎች አብዛኞቹ አድገዋል።

በደረቃማ እና ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች፣ እነዚህ ጥረቶች ማህበረሰቦች የአየር ንብረት ተጽዕኖዎችን በጽናት እንዲቋቋሙ ትልቅ አቅም ይፈጥሩላቸዋል ይላሉ።

በኢትዮጵያ ደን ልማት ውስጥ የብሔራዊ REDD+ ፕሮግራም ዋና አስተባባሪ ይተብቱ ሞገስ (ዶ/ር) የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ እስከ አሁን ካስመዘገባቸው ድሎች መካከል ትልቁ ስኬት የታየው በከፍተኛ ቦታዎች (ደጋማ አካባቢዎች) ላይ መሆኑን ይገልጻሉ።

ትልቁ ስኬት በማህበረሰቡ ዘንድ የአስተሳሰብ ለውጥ መምጣቱ እንደሆነም አመልክተዋል።

የሀገሪቱ ታሪክ ከደን ጭፍጨፋ ወደ ደን ልማት መሸጋገሩን ዋና አስተባባሪው ህብረተሰቡ የደን ጭፍጨፋ የሚያስከትለውን ከባድ ጉዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተረዳው መምጣቱን እና በሀገሪቱ ትልቅ የአስተሳሰብ ለውጥ መፈጠሩን  በአጽንኦት ገልጸዋል።

ዓለም ይህ በመንግሥት የተከናወነው ግዙፍ ሥራ ሊሰጠው የሚገባውን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።  

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ያላት የማያወላውል ቁርጠኝነት በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይበልጥ እየጎላ እና እየሰፋ መጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም