የአፍሪካ ህብረት እና ተመድ ያላቸውን የጋራ ውጥኖች በቁርጠኝነት ለመተግበር እንደሚሰሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ህብረት እና ተመድ ያላቸውን የጋራ ውጥኖች በቁርጠኝነት ለመተግበር እንደሚሰሩ ገለጹ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2019 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሰላም፣ ኢኮኖሚና ፍትሃዊ ዓለምን ለማስፈን በጋራ እያከናወኑ የሚገኘውን ስራ ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታወቁ።
81ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ከመስከረም 8 ቀን 2019 ዓ.ም አንስቶ በኒው ዮርክ እየተካሄደ ይገኛል።
“መተማመንን ዳግም መገንባት እና አዳዲስ ለውጦችን በአግባቡ መምራት፣ ለሁሉም የሚሰራ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን መፍጠር” የጉባኤው መሪ ሀሳብ ነው።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በጉባኤው ላይ ለመታደም ኒው ዮርክ ይገኛሉ።
ከጠቅላላ ጉባኤው ጎን ለጎን ስትራቴጂካዊ ትብብር ማጎልበት፣ የሰላምና ደህንነት ማዕቀፎችን ማጠናከርና አፍሪካን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ሪፎርሞች ላይ ያተኮረ ከፍተኛ የምክክር መድረክ ተካሄዷል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ እና የተባበበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ መድረኩን በጋራ መርተውታል።
ስብስባው ሁለቱ ተቋማት አፍሪካ መዋቅራዊ ፈተናዎችን ለመፍታት እያደረገች ያለቻቸውን ጥረቶች ለመደገፍና ፍትሃዊ የዓለም ስርዓትን ለመፍጠር ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት ይበልጥ ያረጋገጠ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት መረጃ ያመለክታል።
የዓለም አቀፍ የፋይናንስ አወቃቀርን ማሻሻል፣ ዘላቂ የእዳ አስተዳደር እና የአፍሪካ ሀገራት ከቁልፍ የማዕድን ሀብቶች ይበልጥ ተጠቃሚ ማድረግ ውይይት ከተደረገባቸው አጀንዳዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
ሁለቱ ወገኖች በስብሰባው ላይ የአፍሪካ ህብረት እና የተመድን ትብብር ያለውን ስትራቴጂካዊ ፋይዳ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የተቋማቱ ሶስት ነባር የትብብር ማዕቀፎች በአዲስ መልክ ለማደስ እና እ.አ.አ በ2026 ትግበራው የሚጠናቀቀውን የጋራ ፍኖተ ካርታ የተፈጻሚነት ገደብ ለማራዘም መስራት እንደሚገባ ተመላክቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአፍሪካ ያሉ የሰላም እና የደህንነት ተግዳሮቶችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የአፍሪካ ህብረት ቁልፍ አጋር ሆኖ እንደሚቀጥል ዳግም አረጋግጧል።
የአፍሪካን የሰላምና ደህንነት መዋቅር ማጠናከር፣ ግጭትን አስቀድሞ የመከላከል ዲፕሎማሲና የእርቅ ሂደትን በሚገባ መተግበርና ለአፍሪካ ፈተናዎች አፍሪካዊ መፍትሄዎችን ማረጋገጥ የሚያስችል በቂ አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ በስብሰባው ላይ ተነስቷል።
በውይይቱ በሳሄል ቀጠና፣ በሊቢያ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያሉ ወቅታዊ ጉዳዮችና የሰላም ጥረቶች ተገምግመዋል።
በስብስባው ላይ ግጭቶች፣ በዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ የተፈጠሩ መስተጓጎሎች እና የባህር በር መስመሮችን መዝጋትን ጨምሮ ሌሎች ውጫዊ ሁኔታዎች በአፍሪካ ኢኮኖሚ እና ምግብ ዋስትና ላይ ተጨማሪ ጫና እየፈጠሩ መሆኑ ተነስቷል።
የአየር ንብረት ለውጥ እያደረሰ ያለው ጉዳትም ምክክር ተደርጎበታል።
ሁለቱ ወገኖች በውይይቶች ጠንካራ የጋራ ግብረ መልስ መስጫ ማዕቀፍ ለመፍጠር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የአፍሪካ ህብረት እና ተመድ ፍኖተ ካርታ ዝግጅን ለማጠናቀቅ፣ በአፍሪካ ሀገራት የሰላም ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር፣ የምግብ ዋስትና ተግዳሮቶችን ለመፍታትና ለድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ የአሰራር ማዕቀፎችን ለመቅረጽ በቅርበት እንደሚሰሩ መግለጻቸውን የአፍሪካ ህብረት መረጃ ያመለክታል።
81ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እስከ መስከረም 18 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።