መንግስት ለማዕድን ዘርፍ በሰጠው ትኩረት በድንጋይ ከሰል ዘርፍ ውጤታማ ሥራ እንድናከናውን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮልናል - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለማዕድን ዘርፍ በሰጠው ትኩረት በድንጋይ ከሰል ዘርፍ ውጤታማ ሥራ እንድናከናውን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮልናል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2019 (ኢዜአ)፦መንግስት ለማዕድን ዘርፍ በሰጠው ትኩረትና ድጋፍ በድንጋይ ከሰል ዘርፍ ውጤታማ ሥራ እንዲያከናውን ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረለት ዮ ሆልዲንግ ንግድና ማኑፋክቸሪንግ የተሰኘ ሀገር በቀል ኩባንያ አስታወቀ።
የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት እና የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ቦረዳ ወረዳ የሚገኘውን ዮ ሆልዲንግ የድንጋይ ከሰል ማምረቻና ማጠቢያ ፋብሪካ የሥራ እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል።
ዮ ሆልዲንግ የድንጋይ ከሰል ማምረቻና ማጠቢያ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መኳንንት አለሙ እንደገለጹት፤ ኩባንያው በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች 2 የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካዎችን ገንብቶ እየሠራ ይገኛል።
የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካዎቹ በሰዓት 400 ቶን የታጠበ የድንጋይ ከሰል በማምረት የሀገሪቱን ትላልቅ ኩባንያዎች የግብዓት አቅርቦት ችግር እየፈቱ ይገኛሉ ብለዋል።
ኩባንያው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ቦረዳ ወረዳ በሚገኘው ዮ ሆልዲንግ የድንጋይ ከሰል ማምረቻና ማጠቢያ ፋብሪካው ብቻ በአዲሱ በጀት ዓመት በሁለት ወራት ውስጥ ከ2 መቶ ሺህ ቶን በላይ የድንጋይ ከሰል በማጠብ ለገበያ ለማቅረብ ዝግጁ ማድረጉን አስታውቀዋል።
በዚህም ፋብሪካዎቹ የድንጋይ ከሰል ሀብትን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማበልጸግ ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች አስተማማኝ የኃይል ግብዓት እያቀረቡ ይገኛሉ ብለዋል።
ዮ ሆልዲንግ በያዝነው ዓመት በሁለት የተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ሁለት ግዙፍ የከሰል ማጠቢያ ፋብሪካዎችን ለመገንባት በዝግጅት ላይ የሚገኝ መሆኑን አስታውቀዋል።
የሀገር ውስጥ የምርት ፍላጎትን ሙሉ በሙሉ በመቅረፍ ወደ ውጭ ሀገራት ምርቱን ኤክስፖርት ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ኩባንያው የሚያመርተው ከፍተኛ ጥራት ያለው የታጠበ የከሰል ምርት የፋብሪካዎችን የኃይል ፍላጎት በማሻሻል የነዳጅ ፍጆታን እና የምርት ወጪን እየቀነሰ እንደሆነ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለድንጋይ ከሰል ግዥ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት ኩባንያው ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አስታውቀዋል።
ይህም የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ልማት፣ የኢኮኖሚ ዕድገት እና የውጭ ምንዛሬ ግኝት በማሳደግ ረገድ የጎላ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
መንግስት ለማዕድን ዘርፍ የሰጠው ትኩረትና ድጋፍ በድንጋይ ከሰል ዘርፍ ውጤታማ ሥራ እንዲያከናውን ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረለት ዋና ስራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል።
የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ ኤፍሬም ታደሰ በበኩላቸው፤ ፋብሪካው ለበርካታ ወገኖች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ በመሳተፍም የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።