ቀጥታ፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር የብዝሃ ሕይወትና ሥነ-ምኅዳር ደኅንነትን በማስጠበቅ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እያስገኘ ነው 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2019 (ኢዜአ)፦የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የብዝሃ ሕይወትና ሥነ-ምኅዳር ደኅንነት በማስጠበቅ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እያስገኘ መሆኑን የኢትዮጵያ ብዝኅ ሕይወት ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በ2011 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የጀመረችው ታሪካዊ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም ትልቅ አርአያ መሆን ችሏል።

በዚህ ግዙፍ ሀገራዊ ተነሳሽነት አማካኝነት ባለፉት 8 ዓመታት ውስጥ 56 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለው የሀገሪቱ ስነ-ምህዳር እና ብዝሃ ህይወት በዘላቂነት እንዲጠበቅ የሚያስችል ጠንካራ መሰረት ተቀምጧል።


 

ይህ ሁሉን አቀፍ ጥረት ሀገሪቱ የተፈጥሮ ጸጋዎቿን ጠብቃ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ ለምታደርገው ብሩህ ጉዞ ጠንካራ እና አዲስ መሰረት ጥሏል።

የኢትዮጵያ ብዝኅ ሕይወት ኢንስቲትዩት የደንና ግጦሽ መሬት ዕፅዋት ብዝሀ ህይወት ምርምር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አበራ ስዩም ለኢዜአ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ በዓለም ከታወቁት ከፍተኛ የብዝሃ ሕይወት ሀብት ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት።

እስካሁን በተደረጉ ጥናቶች ከ6 ሺህ በላይ የዕፅዋት ዝርያዎች መለያታቸውንና ከ10 እስከ 12 በመቶ የሚሆኑት በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ ዝርያዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ይህ እምቅ የብዝሀ ህይወት ሀብት መኖር ሀገሪቱ የተለያዩ የምግብ ስርዓቶች እንዲኖራት መደላደል የፈጠረ ከመሆኑም በላይ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም መፍጠሩን ተናግረዋል።

የብዝሀ ህይወት ሀብቶች ለውሃ ሀብት፣ ለስነ ምህዳር መጠበቅ፣ ለባህላዊና ዘመናዊ ህክምና መድኃኒትነት እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት በመዋል ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳላቸው ገልጸዋል።

በመሆኑም የብዝሀ ሕይወት ሀብቶቻችንን ጠብቆ ማቆየት ለሀገር ህልውና ወሳኝ በመሆኑ በልዩ ትኩረት እየተሰራበት ነው ብለዋል።


 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የተጀመረው አርአያነት ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ብዝሃ ህይወትን በመጠበቅ እና የአየር ንብረት ለውጥን በብቃት በመቋቋም ረገድ ከፍተኛ ሚና በመወጣት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ስኬታማ መርኃ ግብር በመጀመሩ ምክንያት ቀደም ሲል የተራቆቱ  ቦታዎች እንዲያገግሙ የተደረገ ሲሆን፣ በሂደትም የጠፉ ዝርያዎች ተመልሰው መተካት በመጀመራቸው የተጎዳው ስነ-ምህዳር እየተስተካከለ መጥቷል ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በተከናወኑት ተግባራት ኢንስቲትዩቱ 26 ሚሊዮን የሚደርሱ የሀገር በቀል የዛፍ ዝርያዎችን በማዘጋጀት ማሰራጨቱን ተናግረዋል።

በዚህም የሀገሪቱን የምግብ ሉዓላዊነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ጠንካራ አቅም እየገነባ ይገኛል ነው ያሉት።

በቀጣይም ለትውልድ የሚተርፍ አረንጓዴ ሀብት የመገንባት ሥራውን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም