ለወጣቶች የስራ እድል በማመቻቸት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ስራ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለወጣቶች የስራ እድል በማመቻቸት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ስራ እየተሰራ ነው
ጎንደር ፤ መስከረም 11/2019 (ኢዜአ)፦ በጎንደር ከተማ የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአካባቢውን ፀጋዎች ያማከለ የሥራ ዕድል ፈጠራ እየተከናወነ መሆኑን የከተማዋ ሥራና ክህሎት መምሪያ አስታወቀ።
መምሪያው የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ማስጀመሪያ ፕሮግራምን አስመልክቶ ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር ውይይት አካሂዷል።
የከተማው ሥራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ ላቀው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ በከተማው የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል።
በተያዘው በጀት ዓመት ከ 46 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሠራ ሲሆን፣ የብድር አቅርቦት እና የመሥሪያ ቦታም እየተመቻቸ መሆኑን ተናግረዋል።
ወጣቶችን ወደ ሥራ ከማስገባት ባለፈ በሙያ ብቁ እና ተወዳዳሪ ሆነው እንዲዘልቁ ለማድረግ ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሥልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት በተሰጡ የሙያ ሥልጠናዎች ከአራት ሺህ 400 በላይ የሚሆኑ ወጣቶች በቀጣሪ ድርጅቶች ውስጥ ቋሚ የሥራ ዕድል ማግኘታቸውንም ጠቅሰዋል።
በዛሬው ዕለት በተጀመረው የሙያ ሥልጠና ደግሞ ከሁለት ሺህ በላይ ወጣቶች በ468 ድርጅቶች የሥራ ላይ ልምምድና ቋሚ ሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገልጿል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ታደሰ በበኩላቸው፤ የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምዱ ዘላቂ ሥራና ገቢ ያላቸው እንዲሆኑ የሚያደርግ እንደሆነ ገልጸዋል።
ወጣቶች በዕውቀትና ክህሎት ላይ ተመስርተው ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህ መሳካት በላቀ ቅንጅትና ትብብር መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የጎንደር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ተስፋሁን መኮንን በበኩላቸው፤ በከተማው ለሚገኙ ወጣቶች የክህሎት ማደራጃና የሥራ ዕድል ፈጠራን የሚያፋጥን የሥራ ላይ ልምምድ ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።
ሥልጠናው የወጣቶችን የክህሎት ክፍተት በመሙላት ስራ ቀጣሪ ድርጅቶችና ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥማቸውን የበቃ የሰው ኃይል እጥረት ለመቅረፍ ሁነኛ መፍትሔ መሆኑንም ገልጸዋል።
ወጣቶቹ በኮሌጁ ለ12 ሳምንት የመጀመሪያ ደረጃ የብቃት ትምህርት እና ስልጠና ከወሰዱ በኋላ ወደ ድርጅቶች በመሄድ ተግባራዊ ልምምድ እንደሚያደርጉም ነው ያስረዱት።
በቀጣይም ገበያው ላይ ያለውን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ መደበኛና አጫጭር ሥልጠናዎችን የመስጠት ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት የግል ድርጅት ባለቤት አቶ ቻላቸው ሰጠኝ በበኩላቸው፤ ከዚህ በፊት በተካሔዱ የሥራ ላይ ልምምዶች 30 ወጣቶችን ያለማመዱ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ለ11 ወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውን ተናግረዋል።
እንደዚህ አይነት የስራ ላይ ልምምድ ተቋማት የሚፈልጓቸውን የሰው ኃይል ለማግኘት በር ከፋች መሆኑንም ነው የጠቀሱት።