ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ትንሳኤ ፤ከትናንት ፈተናዎች ወደ ዛሬ ድሎች

ዘመን ሲለወጥ ወቅቶች ሲተኩ ሁልጊዜም አዳዲስ ተስፋዎች እና እቅዶችን ይዘው ይመጣሉ። ይህ ለውጥ ከቀናት አቆጣጠር ከዘመናት ሽግግር የተሻለ ፋይዳ እንዲኖረው ወቅቱን የሚዋጅ ስራ ማከናወን የግድ ይላል።

ወቅቱ ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት የገነባችውን ሁለንተናዊ የለውጥ ምዕራፍ እና ከማሽቆልቆል ወደ ከፍታ የተደረገውን ድል አድራጊ ጉዞ በግልጽ የሚያሳይ ነው።

የኢትዮጵያ ጉዞ በኢኮኖሚያዊ ውጣ ውረዶች እና በዓለም አቀፍ ጫናዎች የተሞላ ነበር።

ኢትዮጵያን ትናንት የገጠሟት ፈተናዎች ሀገሪቱን ወደ አስቸጋሪ አዙሪት ውስጥ ከተዋት ቆይተዋል። 

የዛሬው እውነታ ግን ከትናንቱ ፈተና ፈጽሞ የተለየ ነው። የቁልቁለቱ ጉዞ ሙሉ በሙሉ ተቀልብሶ ሀገሪቱ በሁሉም ዘርፎች ወደ እውነተኛ የማንሰራራት ከፍታ ተሸጋግራለች።

የዘመን ንጽጽር ማዕቀፉ ትናንት በስጋትና በቁጭት የታጀበውን ጉዞ ከዛሬው የብልጽግና ተስፋ ጋር በማቀናጀት ነገን ብሩህ እያደረገ ይገኛል።

በኢኮኖሚው መስክ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለዚህ ታሪካዊ ከፍታ ትልቅ መሠረት የጣለ ዋናው ምዕራፍ ነው።

ላለፉት አምስት አስርት ዓመታት ሲተገበር የነበረውና ለኮንትሮባንድ እንዲሁም ለጥቁር ገበያ መፋፋም ምክንያት ሆኖ የቆየው የምንዛሬ ተመን ተቀይሯል። በገበያ የሚመራ የምንዛሬ ሥርዓት በይፋ መዘርጋቱ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና የወጪ ንግድን ለማንሰራራት የሚያስችል ሰፊ በር ከፍቷል።

የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዛወር ሂደትም ሌላኛው የገበያ ተወዳዳሪነት ማሳያ ነው። የቴሌኮም ዘርፍ ለውጭ ውድድር ክፍት መደረጉ እና የኢትዮ ቴሌኮም ከፊል አክሲዮን ለሕዝብና ለውጭ ኩባንያዎች መሸጡ የቀድሞውን የቁጥጥር ስርዓት ሰብሮታል። ይህ እርምጃ የአገልግሎት ጥራትን ከማሻሻል ባለፈ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ አዲስ ንቃት ፈጥሯል።

የሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብ ሥርዓትን ዲጂታላይዝ ማድረግ ሌላው የለውጥ ምሰሶ ነው። እንደ ሲቢኢ ብር እና ቴሌብር ያሉ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶች ከመንግሥት አገልግሎቶች ጋር በመቀናጀታቸው የገቢ አሰባሰብ አቅምን በከፍተኛ ደረጃ አሳድገዋል።

በዚህም የተነሳ በውጭ ዕርዳታ እና ብድር ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ የነበረው የሀገሪቱ ገጽታ ተለውጦ የውስጥ አቅምን ማዕከል ያደረገ ፋይናንስ እውን ሆኗል።

ከኢኮኖሚ ማሻሻያው ጎን ለጎን በግብርናው ዘርፍ የታየው እመርታ ሀገሪቱን ከምግብ ዋስትና እጥረት ራስን ወደ መቻልና የምግብ ሉዓላዊነትን ወደ ማረጋገት አሸጋግሯታል። በኢትዮጵያ የመስኖ ልማት ጉዞ ቀደም ሲል ከነበረበት መጓተት ወጥቶ የመስኖ ሽፋን ከነበረበት 490 ሺህ ሄክታር ወደ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር ከፍ ማለቱ ታሪካዊ ስኬት ነው።

በበጋ ስንዴ ልማት የተመዘገበው ድል ሀገሪቱ ከውጭ ታስገባው የነበረውን ስንዴ ሙሉ በሙሉ ማስቆም እንድትችል አድርጓታል።

ከዚህም አልፎ ምርቱን ለጎረቤት ሀገራት መላክ መጀመሯ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን በተግባር ያረጋገጠችበት ማሳያ ነው። ግብርናው ከባህላዊ የዝናብ ጥገኝነት ተላቆ የሀገሪቱ የዕድገት አንቀሳቃሽ ሞተር ወደመሆን እየተሸጋገረ መጥቷል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ብቻ ሳይሆን ለኢኮኖሚና ማህበራዊ ከፍታ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ባለፉት ስምንት ዓመታት 56 ቢሊዮን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ ይህ መርሐ ግብር ለፍራፍሬ ልማት እና ለቡና ምርታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረጉ የገበሬውን ገቢ አሳድጓል። ተራቁተው የነበሩ መልክዓ ምድሮች አረንጓዴ እና ለምለም ገጽታን ተላብሰዋል።

የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርም የእንስሳት ተዋጽኦን በቤት ውስጥ ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን አረጋግጧል።

ወተት፣ ሥጋ፣ ማር እና እንቁላል እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬዎች በስፋት እንዲመረቱ በማድረግ  የዜጎችን የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን ለማሳደግ ተችሏል።

በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ "ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ ያመጣው ለውጥ የላቀ ነው። ቀደም ሲል በጥሬ ዕቃ እጥረትና በኃይል መቆራረጥ አሽቆልቁለው የነበሩ የአገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች በፋይናንስና በፖሊሲ ተደግፈዋል።

80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወደ ሙሉ ማምረት አቅማቸው በመመለሳቸው የሀገር ውስጥ ምርት እያደገ መጥቷል።

በከተሞች የተከናወነው የኮሪደር ልማት የዕድገቱ ሌላኛውመገለጫ ነው። በአዲስ አበባ የተጀመረውና ወደ ክልል ዋና ዋና ከተሞች የተሻገረው ይህ ልማት የከተማ መሠረተ-ልማትን አዘምኗል።

የእግር መንገድ፣ የብስክሌት መስመር፣ አረንጓዴ ስፍራዎች እና ውብ መዝናኛዎች መዘርጋታቸው ከተሞችን ለኑሮ፣ ለንግድ እና ለቱሪስት መስህብነት ምቹ አድርጓቸዋል።

በዲፕሎማሲው መስክም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያሳየችው ተፅዕኖ ፈጣሪነት የላቀ ከፍታ ላይ ደርሷል።

ሀገሪቱ በዓለም ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ኢኮኖሚዎች ስብስብ የሆነው የብሪክስ አባል መሆኗ የመደራደር አቅሟን አጠናክሮታል።

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ እና ተጠናክሮ የቀጠለው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ የቀጣናው የትስስር ማዕከልነቷን አረጋግጧል።

የፖለቲካው ትርክት ከብሔር ማዕከልነት ወደ ሃሳብ እና መርህ መር ፖለቲካ መሸጋገሩ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን አጽንቷል።

ይህ የሐሳብ እና የፖለቲካ ሽግግር ዜጎች በልዩነት ውስጥ በአብሮነት እንዲቆሙ እና ለሀገራዊ የጋራ ግቦች እንዲሰለፉ ትልቅ እገዛ አድርጓል።

አዲሱ ዓመት አዲስ መንግስት የሚደራጅበት፣ አዳዲስ ሀገራዊ ግቦች የሚቀመጡበት እና የኢትዮጵያ ህዝብ ለላቀ ውጤት ራሱን የሚያዘጋጅብበት ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።

ሕዝቡ ባለፉት ዓመታት የጣለውን የሰላም እና የልማት መሠረት በማስቀጠል፣ ለሀገሩ የብልጽግና ጉዞ እየሰራ ይገኛል።

ይህ የዘመን ሽግግር የትናንቱን ታሪካዊ ቁልቁለት ሰብሮ ኢትዮጵያን ወደ ብሩህ የማንሰራራት እና የብልጽግና ከፍታ የወሰደ እውነተኛ የድል ማሳያ ነው።

ሕዝብ እና መንግስት በጋራ በመሰለፍ የነገዋን የኢትዮጵያ ከፍታ እውን እያደረጉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም