ዩኒቨርሲቲው የሚያካሄደው የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው የሚያካሄደው የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ እያደረገ ነው
ሮቤ፤ መስከረም 11/2019 (ኢዜአ)፦ የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የሚያካሄዳቸው የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ብርሃነመስቀል ጠና (ዶ/ር) ገለጹ።
ዩኒቨርሲቲው የጭብጥ ተኮር የምርምርና ማህበረሰብ ልማት ንድፈ ሀሳቦችን የሚገመግም የአቅም ግንባታ ዐውደ ጥናት እያካሄደ ነው።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ብርሃነመስቀል ጠና (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን ለማህበረሰቡ ችግሮች መፍትሔ የሚያመላክቱ ምርምሮችን እያካሄደ ይገኛል።
በተለይም የዩኒቨርሲቲው የልህቀት ማዕከል የሆኑት የግብርና፣ ጤና፣ ቱሪዝም፣ ብዝሃ-ሕይወትና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዘርፎች ዋና ዋና የምርምር ትኩረት መስኮች መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው ምሁራንም ባለፉት ዓመታት ባካሄዷቸው የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች የበርካታ ዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እመርታዊ ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል።
በተለይም በግብርናው የኩታ-ገጠም አሰራር፣ በካንሰር ህክምናና ህብረተሰቡን ግንዛቤ በማስጨበጥ ረገድ በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ዩኒቨርሲቲው የሚያከናውናቸው የምርምርና ማህበረሰብ ልማት አገልግሎቶች የህዝብን ችግሮች በተሻለ ሁኔታ ለመፍታት እንዲችሉ በዘርፉ ለተሰማሩ ተመራማሪዎችና ገምጋሚዎች የሚሰጠው ቀጣይነት ያለው የአቅም ግንባታ ስልጠናም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሬዝዳንቱ አውስተዋል።
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ፣ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት በዛብህ ወንድሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአቅም ግንባታ ዐውደ ጥናቱ በምርምር ዘርፍ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በመለየት የተሻለ ተፅዕኖና ውጤት የሚያመጣ ምርምር ለማከናወን እንደሚረዳ ገልጸዋል።
በተለይም ተመራማሪዎቹ በስልጠናው ቆይታቸው በጭብጥ ተኮር የምርምር ንድፎች ምንነትና አዘገጃጀት፣ በማህበረሰብ ተኮር ልማት ስራዎች ንድፈ-ሀሳብ አዘገጃጀትና በዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ በቂ ግንዛቤ እንደሚያገኙ ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው ምሁራን በ2018 የበጀት ዓመት በተለያዩ የትኩረት መስኮች ላይ ያተኮሩ ከ24 በላይ ምርምሮችን ማካሄዳቸውን በማስታወስ፤ በአዲሱ የበጀት ዓመት ደግሞ 96 የምርምር ንድፈ-ሀሳቦች ለግምገማ መቅረባቸውን አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው የሚያካሄዳቸው የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች የአካባቢውን ህብረተሰብ ችግሮች በመቅረፍ ተጠቃሚነቱን ይበልጥ ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።