ቀጥታ፡

በክልሉ የከበሩ ማዕድናትን በማልማት የውጭ ምንዛሬ ለማዳን ትኩረት ተደርጓል

ባህር ዳር ፤ መስከረም 11/2019 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በማዕድን ዘርፍ ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬን ለማዳን የሚያስችሉ ተግባራት ተለይተው በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ማዕድን ቢሮ ገለጸ።

የማዕድን ሃብት ልማት በሃገራዊ ኢኮኖሚ ግንባታው ሚናውን እንዲወጣ በመንግስት ትኩረት ከተሰጣቸው አምስት ዋና ዋና የልማት  ዘርፎች አንዱ ሆኖ እየተሰራበት ይገኛል።

በዚህም መሠረት በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ በማዕድን ዘርፍ ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬን ለማዳን የሚያስችሉ ተግባራት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ወደ ሥራ መገባቱም ተገልጿል።


 

የቢሮው የህዝብና ሚዲያ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዝናው አበበ ለኢዜአ እንዳሉት፤  የማዕድን ሃብቱን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በጥናትና ምርምር ከመለየት ባለፈ ወደ ልማት በማስገባት ከፍተኛ መሻሻል ተመዝግቧል።

በተለይ የዘርፉ  ምሁራንን በማሳተፍ በተካሄደ  ሃብቱን የመለየት ጥረትም ወርቅን ጨምሮ ከፍተኛ መጠን ያለው የኮንስትራክሽን ፣ የኢንዱስትሪ፣ የሃይልና መሰል ግብአት የሚውሉ ማዕድናት መገኘታቸው ነው የተገለፀው።

በሃገራዊ ኢኮኖሚ እድገቱ ማበርከት ያለበትን ሚና በመወጣት በኩል ተስፋ ሰጭ ውጤት እየተገኘ መምጣቱን ገልፀዋል።

ውጤቱን ይበልጥ ለማሳደግም በዚህ በጀት ዓመት ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ በማሳደግና ተኪ ምርቶችን አምርቶ የውጭ ምንዛሬ  በማዳን በኩል በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ 84 ሺህ 800 ኪሎግራም በላይ ወርቅን ጨምሮ እሴት የተጨመረበት የኦፓል ማዕድን አምርቶ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ175 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ጠቅሰዋል።


 

እንዲሁም  ከ7 ነጥብ 9 ሚሊዮን ቶን በላይ የተለያዩ አይነት ተኪ የማዕድን  ምርቶችን በሃገር ውስጥ አምርቶ በመጠቀም ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ የማዳን ስራ ይሰራል ነው ያሉት።

ክልሉ እምቅ የሆነ የከበሩ ማዕድናት ባለቤት እንደሆነ አንስተው፤ እቅዱን ለማሳካትም  በተደራጀ አግባብ እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በክልሉ ባለፈው በጀት ዓመት ወደ ውጭ ሃገራት ከተላኩ የከበሩ ማዕድናት ከ18 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ  መገኘቱንም አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም