የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ተጨባጭ ውጤቶችን ያስገኙ እመርታዎች - ኢዜአ አማርኛ
የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ተጨባጭ ውጤቶችን ያስገኙ እመርታዎች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2019 (ኢዜአ)፦በቡናው ዘርፍ ተግባራዊ የተደረጉ የለውጥ እርምጃዎች የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ተጨባጭ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ማስቻላቸውን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ገልጿል።
የቡና ገበያ ሰንሰለቱን ማሳጠር እንዲሁም ጥራት ላይ የተሰሩ ሥራዎች ከቡና የሚገኘው ገቢ እንዲጨምር መሰረት መጣሉንም ባለሥልጣኑ አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ኢትዮጵያ በቡናው ዘርፍ ተግባራዊ ያደረገቻቸው አዳዲስ ስልቶች ተጨባጭ ስኬቶች እያመዘገቡ ነው።
ለአብነትም በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት 3 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 3 ነጥብ 13 ቢሊዮን ዶላር ተግኝቷል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ይህም ከእቅዱ በላይ ነው ብለዋል።
ደረጃቸው ዝቅ ያሉ ቡናዎች ከገበያው ሥርዓት እንዲወጡ መደረጉን አመልክተው፤ኮሜርሻል ቡናዎች ወደ ስፔሺያሊቲ ቡና ከፍ እንዲል በማድረግ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ መዝለቅ መቻሉን ተናግረዋል።
አርሶ አደሮች በቀጥታ ቡናን ወደ ውጭ መላክ እንዲችሉ የሚያበረታታ አሰራር መዘርጋቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ በቀጥታ ወደ ውጭ መላክ የማይችሉ ደግሞ አቀነባብረው ለሚልኩ ላኪዎች በቀጥታ ማቅረብ የሚችሉበት ሁኔታ ተመቻችቷል ብለዋል።
ይህም የግብይት ሰንሰለቱን ማሳጠር ማስቻሉን ጠቁመው፤ በሂደቱ የሚባክነውን ምርት በመቀነስ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።
ከውጭ የሚገኘው የቡና ምርት የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንዲጨምር አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ተናግረዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የቡና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
ከአምስት ዓመታት በፊት በዓመት የሚመረተው ቡና ከ 500 ሺህ ቶን አይበልጥም ነበር ያሉት አዱኛ (ዶ/ር)፤በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ቡና መመረቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በ2019 በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከሚላከው የቡና ምርት 4 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ጠቁመዋል።
ይሄንን ግብ ለማሳካትም አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ መገባቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የገበያ መዳረሻዎችን የማስፋት ጉዳይ በልዩ ትኩረት እየተሰራበት ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት እስከ 66 ሀገራት የኢትዮጵያን ቡና እየተረከቡ መሆኑን አስታውሰው፤በተለያዩ ሀገራት ያሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንጽላዎች የኢትዮጵያን ቡና በማስተዋወቅ ረገድ አበረታች ሥራዎች እያከናወኑ እንደሚገኝ ተናግረዋል።