የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በትግራይ ቴሌቪዥን ላይ እገዳ ጣለ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በትግራይ ቴሌቪዥን ላይ እገዳ ጣለ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በትግራይ ቴሌቪዥን (Tigray TV) ላይ ላልተወሰነ ጊዜ እገዳ መጣሉን አስታወቀ።
በኢፌዴሪ መንግሥት እና በሕወሓት መካከል በፕሬቶሪያ የተፈፀመውን የሰላም ስምምነት ተከተሎ፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ባደረገው ውይይትና በተደረሰበት ስምምነት መሠረት፣ቀደም ሲል በትግራይ ቴሌቪዥን ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ ተነስቶ ወደ ሥራ መመለሱን በመግለጫው አስታውሷል።
ከዚህም በተጨማሪ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ለትግራይ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞችና ባለሙያዎች የሰላም ግንባታና የሙያ ብቃት ማሳደጊያ ሥልጠናዎችን በመስጠት ሚዲያው ወደ ሕገ-መንግሥታዊና ሙያዊ መስመር እንዲመለስ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አመልክቷል።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የትግራይ ቴሌቪዥን በተሰጠው ዕድል ተጠቅሞ እና የሙያ ሥነ-ምግባር አክብሮ አገልግሎት መስጠት ሲገባው፤ የሀገርንና የህዝብን ደህንነት እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅምን አደጋ ላይ የሚጥሉ፣ወደ ግጭት የሚገፋፉ እና ፅንፈኝነት የሚያበረታቱ መልእክቶች በተከታታይ እየተላለፉበት እንደሚገኝ የባለሥልጣኑ የሚዲያ ይዘት ክትትል ግምገማ ውጤት እንደሚያሳይ ተጠቅሷል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በህግ የተጣለበትን ኃላፊነት መሠረት በማድረግ፣ ከዛሬ ጀምሮ በትግራይ ቴሌቪዥን ላይ ላልተወሰነ ጊዜ እገዳ መጣሉን ገልጿል።
ማንኛውም ዲጂታል፣ የብሮድካስትም ሆነ የሕትመት ሚዲያ የትግራይ ቴሌቪዥንን እንደ መረጃ ምንጭ መጠቀም ወይም የቴሌቪዥን ጣቢያው በህገወጥ መንገድ የሚያሰራጫቸውን ይዘቶች አሰራጭቶ ወይም አስተጋብቶ መገኘት በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን አስገንዝቧል።
ይህንን መመሪያ ተላልፎ በሚገኝ ማንኛውም ሚዲያ ላይ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃዎች እንደሚወስድ በጥብቅ አሳስቧል።