"ያሆዴ"- ከፉሊት ታኮ ብስራት እስከ ዘራሮ ይዞ ጥየቃ - ኢዜአ አማርኛ
"ያሆዴ"- ከፉሊት ታኮ ብስራት እስከ ዘራሮ ይዞ ጥየቃ
(በማሙሽ ጋረደው ከኢዜአ ሆሳዕና ቅርንጫፍ)
በሀዲያዎች ዘንድ በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረው "ያሆዴ" የመተሳሰብና የመረዳዳት ተምሳሌት ነው። በዓሉ ማኅበራዊ መሠረትን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል። "ያሆዴ" አሮጌውን ዓመት ሸኝተው አዲስ ዘመን የሚቀበሉበት፣ የመጻኢ ተስፋ ብስራትና የልምላሜ ምልክት ተደርጎም ጭምር ይቆጠራል።
በመሆኑም በዓሉ ሲቀርብ የሀዲያ ተወላጆችና የበዓሉ ተሳታፊዎች ከሀገር ውስጥም ሆነ ከወጭ ከያሉበት ወደ አካባቢያቸው ይሰባሰባሉ። የያሆዴን ባህላዊ ክዋኔዎች ለመከወን እንዲመች ታስቦ በተዘጋጀው ስፍራ (ሀድይ ነፈራ) ተሰባስበው በዓሉን በድምቀት ያከብራሉ።
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የሶሾሎጂ ትምህርት መምህርና የበዓሉ ተመራማሪ መምህር ታረቀኝ ኑክሮ እንደሚናገሩት፣ የሀዲያ የዘመን መለወጫ በዓል "ያሆዴ" የመተሳሰብና የመረዳዳት ተምሳሌት ነው። በዓሉ የብሩህ ተስፋ፣ የሰላም፣ የፍቅር፣ የረድኤትና የበረከት ተምሳሌት በመሆኑ የተለየ ትርጉምና ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል። በዓሉ ሲከበር በተለያዩ ምክንያቶች ተራርቀው የሚኖሩ የቤተሰብ አባላት ከያሉበት እንደሚሰበሰቡም አመልክተዋል።
በዓሉ ባማረ መልኩ እንዲከበርም ሁሉም የቤተሰብ አባላት የየራሳቸውን የሥራ ድርሻ የሚያከናወኑ ሲሆን፣ አባወራዎች ለበዓሉ ሠንጋ መግዣ የሚሆን ገንዘብ "በቱታ" ወይም በቅርጫ ቡድናቸው አማካኝነት እየቆጠቡ ይቆያሉ። እንዲሁም ለእንስሳት የሚሆን የግጦሽ ሣር የሚያበቅል ቦታ ከልለው ያዘጋጃሉ። ይህ የሚሆነበት ምክንያት ደግሞ በዓሉ በሚከበርበት ሰሞን የሰው ልጅ ይቅርና እንስሳትም መጥገብ አለባቸው ተብሎ ስለሚታመን ነው።
እናቶች በዓሉ ከመቃረቡ ከ3 እና 4 ወራት አስቀድመው ለሥጋ መብያ የሚሆን እንሰት በመፋቅ ቆጮ፣ ቡላና የቅቤ እቁብ (ዊጆ) በመግባት ቅቤ የማጠራቀም ኃላፊነታቸውን በመወጣት ቅድመ ዝግጅት ያደርጋሉ። ለበዓሉ ማድመቂያ የሚሆን ጠጅና ቦርዴን ጨምሮ ሌሎች መጠጦችን ማዘጋጀትም የእናቶች ድርሻ ነው።
በዚህ ወቅት ወጣቶችም የራሳቸው የሆነ የሥራ ድርሻ አላቸው። ወጣት ሴቶች የቤቱን ወለል ይደለድላሉ፣ ያሰማምራሉ፤ የተለያዩ ውበት በሚሰጡ ቀለማት በመጠቀም የቤቱን የውስጥና የውጭ ግድግዳዎች በተለያዩ ጌጦች ያስውባሉ። ወጣት ወንዶች ደግሞ ከነሐሴ መግቢያ ጀምሮ በወላጆቻቸው የተለየላቸውን ግንድ ቆርጠው ለምግብ ማብሰያነት የሚውል የማገዶ እንጨትና ለችቦ (ሳቴ) እንጨት ማዘጋጀት ደግሞ ተግባርና ኃላፊነት ነው። በተጨማሪም አቅመ ደካማ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተናጠልና በቅንጅት የተሟላ ድጋፍ የማድረጉ ሥራ በማኅበረሰቡ ከሚደረጉ የቅድመ ዝግጅት ሂደቶች አንዱና ዋነኛው ነው።
እንደ መምህር ታረቀኝ ማብራሪያ፣ ከነሐሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ የዋሽንት (ገምባቡያ) ድምፅና በታዳጊ ልጆች "ኦሌ... ኦሌ" የወጣቶች ጭፈራ መሰማት ከጀመረ፣ በሀዲያዎች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቀው የዘመን መለወጫ "ያሆዴ" በዓል የመቃረቡ ምልክት ነው። ይህ ባህላዊ ሥነ-ሥርዓት የአዲስ ዘመን ማብሰሪያ (ፉሊት ታኮ) ይባላል። ይህም በዓሉ መቃረቡን ተከትሎ የሚፈጸም ባህላዊ ክዋኔ ነው። ማኅበረሰቡ አሮጌውን ዓመት ሸኝቶ አዲሱን ዓመት ለመቀበል ሲያከናውን የነበረውን ቅድመ ዝግጅት ይበልጥ በማጠናከር መነቃቃት የሚፈጠርበት የብስራት ወቅት ነው።
ወጣቶች "ኦሌ... ኦሌ" እየጨፈሩ በየቤቱ እየዞሩ አዲሱ ዓመት መቃረቡን ያበስራሉ፤ ይበላሉ፣ ይጠጣሉ፤ እንዲሁም የተለያዩ ስጦታዎችን ይቀበላሉ። ይህም ወጣቶቹ ወላጆቻቸው ለዋዜማው በመድረሳቸው መልካም ምኞታቸውን የሚገልጹበት ወቅትም ነው።
ከበዓሉ ዕለት በፊት ያለው የመጨረሻ ገበያ "የእብድ ገበያ" (መቻዕል ሜራ) የሚል ስያሜ አለው። ስያሜው በዓሉ ሲቃረብ በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚፈጠረውን ውጥረት ለማሳየት ያለመ ሲሆን፣ ገበያው በማለዳ ጀምሮ እኩለ ቀን ላይ ይጠናቀቃል።
ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለመግዛትና የያሆዴ በዓል ከተከበረ በኋላ ለአንድ ወር ገበያ ስለማይኖር፣ ይህን ታሳቢ ያደረገ ግብይት ለመፈጸም የግብይት ሂደቱ ጥድፊያ የበዛበት ሆኖ ይታያል። በዚህ ገበያ አባወራዎች በቅርጫ ማኅበራቸው አማካኝነት ያጠራቀሙትን ገንዘብ በመያዝ የእርድ በሬ ይገዛሉ። በዚህ ወቅት ገንዘብ ማጠራቀም ያልቻሉ የቅርጫ አባላት እህል በሚደርስበት ወቅት ለመክፈል ተስማምተው በሬውን በዱቤ (አባ) እንዲገዙ ይደረጋል። ይህም የሚሆነው በ"ያሆዴ" በዓል አንዱ ሲበላ ሌላው ተመልካች መሆን ስለሌለበት ነው።
የ"ያሆዴ" በዓል መከበር የሚጀምረው በአተካን ሂሞ ወይም በአተካና ምሽት ሲሆን፣ ይህም ከበዓሉ አንድ ቀን በፊት ያለው ምሽት ነው። በሀዲያዎች ዘንድ ቂምና ጥላቻን ይዞ ወደ አዲሱ ዓመት መሸጋገር ፈጽሞ የማይቻል በመሆኑ፣ ይህንን የበዓል ዋዜማ እርቀ-ሰላም የሚፈጽሙበትና ተራርቀው የቆዩ የአካባቢው ተወላጆች በናፍቆት የሚገናኙበት በመሆኑ ዕለቱን የተለየ ያደርገዋል።
"አተካና" በሀዲያዎች ዘንድ ለክብር እንግዳና በዘመን መለወጫ በዓል ወቅት የሚዘጋጅ ምግብ ነው። አተካና ከወተት፣ ከአይብ፣ ከቡላ፣ ከቅቤና ከሌሎች የቅመማ ቅመም ውጤቶች የሚዘጋጅ ሲሆን፣ በጣም ጣፋጭና የምግብ ፍላጎትን የሚጨምር ምግብ ነው። ሀዲያዎች በበዓሉ ዋዜማ ይህንን የተለየ ምግብ ተሰባስበው በአብሮነት በመመገብ በደመቀ መልኩ በዓሉን ማክበር ይጀምራሉ።
የአካባቢው አባቶች በወጣቶች የተዘጋጀ የማቀጣጠያ እንጨት (ሳቴ) ይዘው ትልቅ በሚባሉ አባወራዎች ቤት ደጃፍ ወደ ተዘጋጀው የችቦ ደመራ (ጦምቦራ) ቦታ ይመጣሉ። የሀገር ሽማግሌዎች አዲሱ ዓመት የብርሃን ዓመት እንዲሆን፣ ለሀገርና ለሕዝቦቿ ሰላም እንዲጸና፣ አብሮነት እንዲጠናከር፣ ሰላምና ፍቅር እንዲነግሥ ፈጣሪያቸውን ከተማጸኑ በኋላ ችቦውን በእሳት ይለኩሳሉ። ችቦው ከተለኮሰ በኋላ የአካባቢው ወጣቶች ተሰባስበው "ያሆዴ... ያሆዴ!... ያሆዴ!... ሆያ!... ሆ!" በማለት እየጨፈሩ ያነጋሉ።
በሀዲያዎች ዘንድ "ያሆ" ማለት የአዲስ ዓመት መግባትን ተከትሎ የሚደረግ ማብሰሪያ ጭፈራ ሲሆን፣ "ኤዴ" ማለት ደግሞ አገናኝ ማለት ነው።
በ"ያሆዴ" በዓል የእርድ ሥነ-ሥርዓት ለማከናወን ነዋሪዎች የሚሰበሰቡበት ስፍራ "ነፈራ" የሚል ስያሜ አለው። ይህም የተለያዩ ማኅበራዊና ባህላዊ ክዋኔዎችን ለመከወን እንዲመች ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ሰፋ ያለ ቦታ ሲሆን፣ በተለያዩ የጥላ ዛፎች የተዋበና ለዚሁ ተግባር የተዘጋጀም ነው።
በዕለቱ ለእርድ የተዘጋጀው ሠንጋ ከቀረበ በኋላ የባህል ሽማግሌዎች የበሬውን ሻኛ በሰርዶ ሣር ለጋ ቅቤ ይቀባሉ፤ ወተትም ያፈሱበታል።
ይህ ባህላዊ ሥነ-ሥርዓት "ጋቢማ" የሚባል ሲሆን የመልካም ምኞት መግለጫ ሥነ-ሥርዓት ነው፦ "ክፉ ቀን አይምጣ፣ ራብና ሰቀቀን ይጥፋ፣ ጥጋብ ይስፈን፣ በአካባቢውና በሀገሩ ጥጃ ይቦርቅ፣ ልጅ ይፈንጭበት፣ ሀገር ሰላም፣ ገበያ ጥጋብ ይሁን፣ ሰማይና ምድሩ ይታረቁን" እያሉ በአባቶች ምርቃት ከተካሄደ በኋላ የእርድ ሥነ-ሥርዓቱ ይከናወናል።
የእርድ ሥነ-ሥርዓቱ የተከናወነበት ቤት እማወራ አስቀድመው ባደረጉት ዝግጅት መሠረት ቅቤ፣ (ቦርዴ፣ ቃሪቦ፣ ጠጅ፣ ብርዝ) እንዲሁም ከታረደው የበሬ ሥጋ አርዚ ማራ (የቅምሻ ሥጋ) ይወሰድና ክትፎ ከተዘጋጀ በኋላ በጋራ እየበሉና እየተጫወቱ ይውላሉ።
በዚህም በቅርጫ ሥጋው ላይ ከሚሳተፉት የቤተሰብ አባላት ውጭ በአካባቢው የሚገኙ አቅመ-ደካማ ወገኖች ጭምር አብረው በመብላትና በመጠጣት በዓሉን በአንድነት ያሳልፋሉ። ቀሪውን የቅርጫ ሥጋም አባላቱ ተከፋፍለው ወደየቤታቸው ይወስዱታል።
በዓሉ አብሮ የመብላት፣ የመጠጣት፣ የመጠያየቅ፣ ችግርንና ግጭትን በጋራ ተወያይቶ የመፍታት፣ መፈቃቀርና መተሳሰብን የሚፈጥር፣ አቅመ-ደካሞችና የተቸገሩ የሚረዱበት የአብሮነት መገለጫ በመሆኑ በተለየ መልኩ ይከበራል።
ከእርድ ሥርዓቱ በኋላ በማግስቱ ልጆች አደይ አበባ (ዘራሮ) ይዘው ወደ ወላጆቻቸው እየጨፈሩ ይመጣሉ። ሥርዓቱም "ሚክር ከጃ" ይባላል። "እንደ መስቀል አበባ ፈክታችሁ ኑሩ" ተብለው ይመረቃሉ። ከሥጋው፣ ከቦርዴውና ከአተካናውም እንዲመገቡ ይደረጋል።
በ"ያሆዴ" የዘመን መለወጫ በዓል ትዳር የያዙ የቤት እመቤቶች ከባሎቻቸው ጋር ሆነው ወደ ወላጆቻቸው ምግብ ሠርተው፣ የሹልዳ ሥጋና አደይ አበባ ጭምር ይዘው ይሄዳሉ። በዓሉ ያላገቡ ወጣቶች የሚተጫጩበትና ለአዲስ ሕይወት ጅማሬ የሚያበስሩበት በመሆኑ የተለየ ድባብም አለው።
የመተሳሰብና የመረዳዳት ተምሳሌት የሆነው የዘንድሮው የ"ያሆዴ" በዓል መስከረም 11 እና 12 ቀን 2019 ዓ.ም. በሆሳዕና ከተማ በተለያዩ ባህላዊ ሥነ-ሥርዓቶች ታጅቦ በደማቅ ሁኔታ ይከበራል።