ቀጥታ፡

የሐረር ከተማ ኮሪደር ልማት -ከውብ ስፍራ እስከ ወጣቶች የንባብ ማዕከልነት

ታሪካዊቷና ውቧ የሀረር ከተማ አሁን ላይ የከተማ ገጽታዋን የሚቀይሩ ሰፋፊ የኮሪደር እና የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን በማከናወን ላይ ትገኛለች።

እነዚህ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችና የመናፈሻ ግንባታዎች ከተማዋን ለነዋሪዎቿና ለጎብኚዎቿ ምቹ፣ ውብና ማራኪ ከማድረጋቸው ባሻገር፤ የከተማዋ ወጣቶች እውቀት የሚሸምቱበት፣ የሚያነቡበት እና አዳዲስ ሀሳቦችን የሚያፈልቁበት የንባብ ባህል ማጎልበቻ ስፍራዎች እየሆኑ መጥተዋል።


 

የኮሪደር ልማቱ ያመጣው ትልቅ ለውጥ የቦታዎቹ አገልግሎት ከውበትና ከመዝናናት አልፎ ወደ እውቀት ማዕከልነት መሸጋገሩ ነው። አረንጓዴ ስፍራዎቹና መናፈሻዎቹ ለወጣቶችና ለተማሪዎች የተረጋጋ፣ ነፃ እና ለንባብ ተስማሚ ከባቢን ፈጥረዋል።

በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የ4ኛ ዓመት የጋዜጠኝነትና ሥነ-ተግባቦት ተማሪ የሆነችው ዕድላዊት በቀለ እንደምትታዘበው፣ በኮሪደር ልማቱ የለሙት ስፍራዎች ወጣቶች በነፃነት የሚያነቡበት፣ ሀሳብ የሚያፈልቁበትና ማኅበራዊ ትስስር የሚፈጥሩበት ምቹ አየር ፈጥረዋል። በተጨማሪም ለዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎችና ለማህበራዊ ድረ-ገጽ ምስል ቀረጻዎች ውብ ከባቢን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አዎንታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል።


 

በተመሳሳይ፣ ወጣት ናሆም ጌታቸው እንደሚያመለክተው፤ በከተማዋ የተገነቡት መናፈሻዎችና አረንጓዴ ስፍራዎች የወጣቶችን የማንበብ፣ የማሰብና የማስላት አቅም ከማጎልበት ባለፈ የፈጠራ ችሎታንና ማኅበራዊ ተሳትፎን በማጠናከር ረገድ የጎላ ድርሻ አላቸው።


 

ቀደም ሲል በከተማዋ ለወጣቱ ተስማሚ የመዝናኛና የማሰቢያ ስፍራዎች እጥረት በመኖሩ፣ በርካታ ወጣቶች ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታዎች ለማሳለፍ ይገደዱ እንደነበር የከተማዋ ነዋሪዎች ያነሳሉ። የኮሪደር ልማቱ ግን ይህንን ማህበራዊ ክፍተት በመድፈን ወጣቱን ከአልባሌ ስፍራዎች በመታደግ ወደ እውቀትና ምርታማነት አዞሮታል።

ወጣት እዮብ አበበ እና ወጣት የአብስራ ደሳለኝ እንደሚያስረዱት፤ በኮሪደር ልማቱ የተገኙት አዳዲስ ስፍራዎች ለወጣቱ ከመዝናኛነትና ከስራ እድል ፈጠራ ባሻገር፣ የእውቀት መገበያያና የንባብ ባህል ማዳበሪያ በመሆን ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለንባብና ለዕውቀት ማግኛ ተስማሚ ከባቢ መፈጠሩ ለትውልድ ግንባታው ትልቅ ስኬት ነው።


 

የሐረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሊድ አብዲ እንደሚገልፁት፣ በከተማዋ የተገነቡት ሰፋፊ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከተማዋን ውብና ለጎብኚዎች ምቹ ከማድረግ ባሻገር፤ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ለወጣቱ ደግሞ የመዝናኛ፣ የንባብ፣ የፈጠራ እና የእውቀት ማዕከል በመሆን ማህበራዊ ፋይዳቸውን አረጋግጠዋል።

በከፍተኛ ወጪ የተገነቡትንና ለህብረተሰቡ መጠነ-ሰፊ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙትን እነዚህን የኮሪደር እና የአረንጓዴ ስፍራዎች ተንከባክቦ ማቆየት የሁሉንም ወጣቶችና የህብረተሰብ ክፍሎች ንቁ ተሳትፎና ሀላፊነት የሚጠይቅ በመሆኑ፣ የተገኙትን እሴቶች በመጠበቅ ረገድ የተቀናጀ ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም