ኢትዮጵያ እና የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ትብብራቸውን በጠንካራ መሰረት ላይ አጽንተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ትብብራቸውን በጠንካራ መሰረት ላይ አጽንተዋል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2019 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ እና የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር በጠንካራ መሰረት ላይ በማጽናት ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገሩን በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ገለጹ።
በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሁለቱ አገራት ጠንካራና እያደገ የመጣ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ያላቸው አገራት ናቸው።
በተለይም አሁን ላይ በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራውን ተከትሎ በአገራቱ መካከል ያለው ኢኮኖሚያዊ ትብብር ለማጠናከር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል።
መንግሥት የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብና አገሪቱ ከውጭ ዓለም ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት እንድትተሳሰር የሚያደርጋቸውን ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ኤምባሲው እያስተዋወቀ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን፣ በቂ ታዳሽ የኃይል አቅርቦት፣ ወጣት የሰው ኃይል እና ስትራቴጂክ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እንዳላት አንስተዋል።
ከተቀረው ዓለም ጋር በተለይም በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ከፍተኛ ትስስር እንዳላትና ሌሎች ለኢንቨስትመንት አስቻይ ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
ኤምባሲው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲውን ለማጠናከር የተለያዩ ጉባኤዎች ላይ ከመሳተፍ ጀምሮ ከተለያዩ ኢንቨስትሮች ጋር ውይይቶችና ምክክሮች እስከ ማድረስ የዘለቀ ተሳትፎ እንዳለው ተናግረዋል።
ከዚህ አንጻር ከሰሞኑ በኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የተመራው ልዑክ ቡድን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በተካሄደው ዓመታዊው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ጉባኤ ላይ መሳተፉ ይህንን ጥረት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው አብራርተዋል።
የንግድ ግንኙነቱ እንዲጠናከር አሁን ላይ ያሉ ገበያዎችን ማጠናከርና አዳዲስ የገበያ እድሎችን ማስፋት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
በሌላ በኩል የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲውን ለማጠናከር ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ የቱሪዝም ኃብት በማስተዋወቅና ከተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ወደ ሌሎች አገራት ለቱሪዝም የሚሄደውን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጎብኚ ወደ ኢትዮጵያም እንዲያቀና ለማድረግ እየተሰራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ለዚህም ኢትዮጵያ ያሏትን የቱርዝም መስህቦችና በገበታ ለሀገር የተሰሩትን ጨምሮ ሌሎች የቱሪዝም መዳረሻዎችን በስፋት የማስተዋወቅ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስረተድተዋል።
በሌላ በኩል የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማሳለጥና ሙያዊ ድጋፎችን ለማስፋት የሚያስችሉ የትብብር አድማሶችን የማጠናከር ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም መሰል ሥራዎች ተጠናክረው የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶችና የኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ ለማጽናት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡