ኢትዮጵያ በዓለም የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዓለም የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2019 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ በዴንማርክ ኮፐንሃገን በተካሄደው ሁለተኛው የዓለም የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ለሁለት ቀናት በተደረገው ሻምፒዮና ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል።
በሻምፒዮናው ላይ ከ86 ሀገራት የተወጣጡ ከ450 በላይ አትሌቶች ተሳትፈዋል።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ላይ በወንዶችና በሴቶች ግማሽ ማራቶን፣ በወንዶችና በሴቶች አምስት ኪሎ ሜትር እንዲሁም በሴቶች አንድ ማይል ውድድሮች ላይ ተሳትፎ አድርጋለች።
በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ በአንድ የወርቅ፣ ሁለት የብር እና አንድ የነሐስ በድምሩ አራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ልቅና አምባው በአምስት ኪሎ ሜትር የወርቅ እና ፍሬወይኒ ኃይሉ በአንድ ማይል የብር ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ አስገኝተዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በቡድን በግማሽ ማራቶን ወንዶች የብር እና በግማሽ ማራቶን ሴቶች የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች።
ኬንያ በሶስት የወርቅ፣ ሶስት የብር እና አንድ የነሐስ በአጠቃላይ ሰባት ሜዳሊያዎች በማግኘት የውድድሩ አሸናፊ ሆናለች።
ኤርትራ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች።
በሻምፒዮናው 12 ሀገራት የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ገብተዋል።