ቀጥታ፡

የቦሮ ሺናሻ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ "ጋሪ ዎሮ " በዓል በድምቀት ተከበረ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2019 (ኢዜአ):- የቦሮ ሺናሻ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል “ጋሪ ዎሮ ለአብሮነት እና ለባህል ልማት” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

በበዓሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ አስካለች አልቦሮ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልከድር፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀኔራል አስራት ደኔሮ፣ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ተወካይ ረዳት ፕሮፌሰር  ከፍያለው አብዲሳ እና የብሔረሰቡ ተወላጆችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።


 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አስካለች አልቦሮ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ ጋሪ ዎሮ የይቅርታ፣ የፍቅር፣ የሰላምና የተስፋ በዓል ነው።

በዓሉ ከለውጡ ወዲህ በአዲስ አበባ በደማቅ ሁኔታ መከበሩ ትውልድ ተሻጋሪ ባህልን ለማስቀጠል እና አብሮነትን ለማጠናከር ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ተወካይ ረዳት ፕሮፌሰር ከፍያለው አብዲሳ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የብዝሃ ባህል መገለጫ ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።


 

ሚኒስቴሩ የብዝሃ ባህል ሀብቶችን በማስተዋወቅ ለሀገር ልማት እንዲውሉ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል። 

“ጋሪ ዎሮ” የቦሮ ሺናሻ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ እና እሴት ከተፈጥሮ ጋር ያለው ጥልቅ መስተጋብር የሚንጸባረቅበት መሆኑም አንስተዋል። 

በዓሉ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ የተራራቁ የሚቀራረቡበት እንዲሁም የአንድነት እና የህይወት ትስስር መገለጫ ነው ብለዋል።

በበዓሉ ተሳታፊ የሆኑት በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የአመራርና አስተዳደር መምህር  ሙላቱ  ታከለ (ዶ/ር)፣ በዓሉ ተለያይቶ የቆዩ የሚገናኙበት እና ታላላቆች የሚከበሩበት የአንድነት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

አቶ ማርቆስ ኪትላ በበኩላቸው፣ በተለይም በክረምት ወራት በውሃ ሙላት ምክንያት ተለያይተው የቆዩ ሰዎች እርስ በእርስ በናፍቆት የሚጠያየቁበትና ማህበራዊ ትስስራቸውን የሚያጠናክሩበት አጋጣሚ መሆኑን አስረድተዋል።


 

በዓሉ ከአሮጌው ዘመን ወደ አዲስ ዘመን፣ ተስፋና ተነሳሽነት በይቅርታና በመልካም ብስራት የሚሸጋገሩበት ልዩ እሴት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአካባቢው ተወላጅ አቶ አዲሱ አዳሜ ናቸው ።

በበዓሉ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች፣ አልባሳት፣ የኪነ-ጥበብ ትርኢቶች እና ባህላዊ ጨዋታዎች ለታዳሚው ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም