ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፍትሃዊ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የህልውና እና የቀጣናዊ ደህንነት የማረጋገጥ መሠረት ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2019 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ፍትሃዊ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የብሄራዊ ጥቅም፣ የህልውና፣ የቀጣናዊ ደህንነት የማረጋገጥና ኢኮኖሚያዊ ትስስር የማጠናከር መሠረት ነው ሲሉ ምሁራን ገለጹ። 

የባህር በር ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ፣ በሴራ ያጣችው ይህ ተፈጥሯዊ ሀብቷ አሁን ካለው የህዝብ ቁጥርና ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገቷ አኳያ የህልውና ጉዳይ ሆኗል።

አሁን ላይ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የኢትዮጵያውያን ጥያቄ ብቻ ሳይሆን፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሰፊ ድጋፍ እያገኘ መጥቷል።

ይህ የፍትህና የልማት ጥያቄ የሰላም እና የኢኮኖሚ ትስስር በሚያጠናክር መልኩ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እውን እንዲሆን መንግስት ያላሰለሰ ጥረት ማድረጉን ቀጥሏል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝምና ገቨርናንስ መምህርና ተመራማሪ ተስፋዬ ጂማ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ የቀይ ባህር ጉዳይ ለኢትዮጵያ ከንግድና ገቢ ምንጭነት የዘለለ የሉዓላዊነትና የህልውና ጉዳይ ነው። 

የባህር በር ማግኘት ሀገሪቱ የንግድ ልውውጧን ከማስፋፋት ባለፈ የግብርናና የዓሣ ሀብት ልማቷን ለማሳደግ ወሳኝ ሚና አለው። 

በተጨማሪም ይህ እጅግ አስፈላጊ የጂኦፖለቲካዊ ዕድል በቀጣናውና በዓለም አቀፍ መድረክ የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ተጽዕኖ በከፍተኛ ደረጃ ያጠናክረዋል።

በመሆኑም የቀይ ባህር ተደራሽነት ለሀገሪቷ ሁለገብ ደህንነትና ቀጣይ እድገት ዋስትና የሚሰጥ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑ አንስተዋል።

የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ መሪ ተመራማሪ አቶ ሰለሞን ተፈራ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በትክክል ለመረዳት የታሪካዊ፣ ህጋዊ እና የጂኦፖለቲካ ዳራዎችን መመርመር ይገባል ብለዋል። 

እጅግ ተለዋዋጭ በሆነው የቀጣናው የፀጥታና የፖለቲካ ቁመና ውስጥ የባህር በር ባለቤት መሆን ለኢትዮጵያ የህልውናና የሉዓላዊነት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑም ጠቁመዋል። 

ስለሆነም ምሁራን ለዚህ ሀገራዊ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ አጋዥና አዋጭ ሃሳቦችን በማቅረብ ታሪካዊ ሀላፊነታቸውን መወጣት እንደሚችሉ አስገዝበዋል።

የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ  ከሀገራዊ ጥቅም እና ከህልውናዋ ጋር አያይዞ ማየት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

የሀገሪቷ እያደገ የመጣው ህዝብ ቁጥርና ተለዋዋጭ የጂኦ ፖለቲካ ሁኔታ ጉዳዩን የበለጠ ወሳኝ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

ለዚህም ምሁራን በጥናትና ምርምር የተደገፈ መረጃ በማመንጨት የሀገሪቱን ጥቅም በዓለም አቀፍ መድረኮች በማንሳት እና በማስገንዘብ ለሀገራቸው ብሔራዊ ጥቅም መከበረ አዎንታዊ ሚና ማበርከት እንደሚችሉ ተናግረዋል።

የዓባይ እና የቀይ ባህር ስትራቴጂክ ፎረም ሰብሳቢ  አበበ ገመቹ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የኢትዮጵያን የባህር ባለቤትነት ጥያቄ ጉዳይ ምሁራን በአንድ ተቋም ተሰባስበው በጥናትና ምርምር፣ የፖሊሲ ሀሳቦችን በማመንጨት በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ መድረኮች ሊያሰሙ ይገባል። 

የዓባይ እና የቀይ ባህር ስትራቴጂክ ፎረም ይህንን ዓላማ ለማሳካት የተቋቋመ ስትራቴጂክ ፎረም መሆኑን ጠቅሰው፣ ከጂኦግራፊ፣ ከህዝብ ብዛት፣ ከፍትሃዊነትና ከቀጣናዊ ትስስር አኳያ ጥናቶችን በማካሄድ የሀገሪቱን ጥቅም የሚያስከብሩ ሀሳቦችን እያመነጨ እንደሚገኝ አብራርተዋል። 

የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ጉዳይን ኢትዮጵያ በያዘችው የሰላማዊ ዲፕሎማሲ መንገድ በመቀጠል የባህር ጥያቄዋን በጽኑ ማራመድ መቻሏ የሚደነቅ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም