ቀጥታ፡

የ"ጊፋታ" በዓል ዕሴቶች ለሀገራዊ አንድነትና ልማት ከፍተኛ አበርክቶ አላቸው 

ወላይታ ሶዶ ፤ መስከረም 10/2019 (ኢዜአ):- የወላይታ ዘመን መለወጫ የ"ጊፋታ" በዓል እሴቶች ለሀገራዊ አንድነትና ለልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

የ2019 ዓ.ም የወላይታ ዘመን መለወጫ "ጊፋታ" በዓል "የትውልድን ቅርስ እንጠብቅ፤ የጊፋታን ውርስ እናስቀጥል" በሚል መሪ ቃል በወላይታ ሶዶ ከተማ በተለያዩ ደማቅ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።


 

በበዓሉ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እንደገለጹት፤ በክልሉ እንደ "ጊፋታ" ባሉ በዓላት የሚንጸባረቀውን ብዝሃነትና የአንድነት እሴት ለማስቀጠል በልዩ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

ጊፋታ የዕርቅ፣ የመተሳሰብና የመጋመድ ምልክት እንዲሁም የኢትዮጵያዊያን የጋራ ሀብት መሆኑን ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በዓሉ በዜጎች መካከል ጠንካራ ማህበራዊ ግንኙነት እንደሚፈጥር ጠቁመዋል። 

አክለውም የጊፋታ የዕርቅ ዕሴቶች ለሀገራዊ ሰላምና ልማት ከፍተኛ ድርሻ እንደሚወጡም ተናግረዋል።


 

በተጨማሪም የበዓሉ የመረዳዳትና የደግነት ዕሴቶች ክልሉን የሰላምና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመረውን ጉዞ ዕውን ለማድረግ የሚያግዙ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ከዚህም ባሻገር የክልሉን የቱሪዝም ልማት በመደገፍ፣ ወደ ክልሉ የሚመጡ ጎብኚዎችን ቁጥር በመጨመርና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት አመልክተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ የጊፋታን በዓልና ዕሴቶቹን ጠብቀው ለትውልድና ለዓለም ላበቁ አባቶችና ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል። 

አክለውም በበዓሉ ላይ የታየውን አንድነትና ቅንጅት በሌሎች የልማት ስራዎች ላይም በመድገም ሕዝቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል።


 

"ጊፋታ" የኢትዮጵያ ህዝብና የዓለም ሀብት ነው ያሉት ደግሞ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ ናቸው።

በዓሉ በሰላም፣ በአንድነትና በፍቅር የሚከበር መሆኑን ያመለከቱት ዋና አስተዳዳሪው፤ "ጊፋታ" ሀገራዊ አንድነትንና ህብረብሔራዊነትን በማጠናከር ለጋራ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የበዓሉን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በማጉላት፣ የዓለም ቅርስነቱ ተጠብቆ እንዲቆይ የዞኑ አስተዳደር በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ እታገኝ ኃይለማርያም፤ "ጊፋታ" ጠብና ቁርሾ ተወግዶ፣ በፍቅርና በአንድነት የሚከበር በጎ እሴቶች የሚንጸባረቁበት በዓል መሆኑን ገልጸዋል።


 

በተጨማሪም በዚህ አዲስ መንፈስ በከተማዋ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በማጠናከርና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በማስጀመር፣ ህዝቡን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎችም የ"ጊፋታ"ን ዕሴቶች በመጠበቅና የጋራ አንድነታቸውን በማጠናከር፣ ለጋራ ልማትና እድገት በአንድነት እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

በበዓሉ አከባበር ላይ የፌደራል፣ የክልል፣ የዞን፣ የከተማና የወረዳ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም