ቀጥታ፡

ስፖርታዊ ውድድሮች በሕዝቦች መካከል ያለውን አብሮነት ለማጠናከር የጎላ ሚና አላቸው

ወልቂጤ፤ መስከረም 10/2019 (ኢዜአ):- ስፖርታዊ ውድድሮች ተተኪ ስፖርተኞችን ከማፍራት ባሻገር፣ በሕዝቦች መካከል ያለውን አንድነት፣ የወንድማማችነት መንፈስና አብሮነትን ለማጠናከር የጎላ ሚና እንደሚጫወቱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገለጸ።

6ኛው ዙር የ15 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።


 

በዚህ ወቅት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌታቸው ሌሊሾ፤ ​ስፖርታዊ ውድድሩ የህዝቦችን አንድነት፣ ትብብርና ወንድማማችነት እያጎለበተ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡


 

በአትሌትክሱ ዘርፍ ተተኪ ስፖርተኞችን በማፍራት ረገድ መድረኩ ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

አክለውም ውድድሩ የክልሉን የቱሪዝም አማራጮች ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን ገልጸዋል።

​የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟ ጎልቶ እንዲወጣ ዞኑ ጠንካራ አትሌቶችን በማፍራት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።


 

​በዞኑ ባህል እየሆነ የመጣው የአትሌትክስ ስፖርት የህዝቦችን አንድነትና ሰላም ለማጎልበትና አካላዊና አእምሮአዊ ጤንነትን ለመጠበቅ እያስቻለ ነው ብለዋል።

የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር በበኩላቸው የጎዳና ሩጫ ከስፖርታዊ ውድድርነት ባሻገር ወልቂጤ ከተማን በስፖርት ቱሪዝም፣ በኢንቨስትመንትና በማህበራዊ ዘርፍ ለማነቃቃት ያስችላል ብለዋል።


 

ውድድሩ ኢትዮጵያዊነትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርንና አንድነትን የሚያጠናክር መድረክ መሆኑን ነው የጠቀሱት፡፡

የኬሮድ የጎዳና ሩጫና ልማት አክስዮን ማህበር ሰብሳቢ አትሌት ተሰማ አብሽሮ “ኬሮድ የጎዳና ላይ ሩጫ“ ከሃገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉ አዳዲስና ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በውድድሩ በወንዶች አትሌት አባይነህ አየን 1ኛ ሲወጣ በሴቶች ደግሞ ማርታ ገብረ ሚካኤል ውድድሩን በአንደኝነት አጠናቃለች፡፡

በወድድሩ 1ኛ ለወጣው 200 ሺህ ብር እንዲሁም እስከ ስድስተኛ ደረጃ ለወጡ አትሌቶች ሽልማት ተበርክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም