ከሀገር የተዘረፉ ቅርሶችን በጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በማስመለስ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል - ኢዜአ አማርኛ
ከሀገር የተዘረፉ ቅርሶችን በጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በማስመለስ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 10 /2019(ኢዜአ)፡- በተለያዩ ምክንያቶች የተዘረፉ ጥንታዊ ቅርሶችን በጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ወደ ሀገር በማስመለስ ረገድ ተጨባጭና አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ተመራማሪና የኢትዮጵያ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባል አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) ገለጹ።
ኢትዮጵያ በጦርነት፣ በዝርፊያና በተለያዩ ምክንያቶች ቀደም ሲል ያጣቻቸውን ጥንታዊ ቅርሶች በጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በመታደግና በማስመለስ ረገድ በተለይም የመደመር መንግሥት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀሱ፣ ተጨባጭና አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በዚህም ባለፉት ሰባት ዓመታት ብቻ በርካታ ጥንታዊ ቅርሶች በዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ወደ እናት አገራቸው ተመልሰዋል።
ተመራማሪና የኢትዮጵያ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባል አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ አግባብ ባልሆነ መንገድ በኃይልና በዘረፋ የተወሰዱ ቅርሶች ሁልጊዜም ወደ መጡበት የታሪክ ባለቤት መመለስ እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ በተለያየ አጋጣሚ ሕገወጥ በሆነ መልኩ የወጡባትን ቅርሶች ለማስመለስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተቀናጀ መልኩ እየሰራች መሆኑንም አብራርተዋል።
በተለይም ቅርሶቻችን በተለያዩ የውጭ አገራት ገበያዎችና ለጨረታ ሽያጭ በሚቀርቡበት ወቅት፣ ሕጋዊና ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ተቃውሞዎችን በማቅረብ ጨረታዎቹ ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዙ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ጨረታዎቹ ከተሰረዙ በኋላም መንግሥትና ባለድርሻ አካላት በአነስተኛና በተመጣጣኝ ዋጋ በመደራደር በርካታ ታሪካዊ ቅርሶችን መታደግ መቻሉንም አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅትም ከመቅደላ ተዘርፎ በአንድ ኦስትሪያዊ ድርጅት አማካኝነት አቡዳቢ ላይ ለሽያጭ የቀረበውን የዓጼ ቴዎድሮስ ወንጌል ለማስመለስ መንግሥት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
በተጨማሪም ከዓለም አቀፍ ሙዚየሞች ጋር በቀጥታ በመደራደር ቅርሶችን ማስመለስ ሌላው ውጤታማ ስልት ሆኖ በመተግበር ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ አሠራር መሠረት የአሜሪካው ቶሌዶ ሙዚየም ከግለሰብ የተቀበላቸውን ወደ 380 ገደማ የኢትዮጵያ ቅርሶች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ስምምነት ላይ መደረሱን አመልክተዋል።
በቅርቡ ሁለት የ15ኛው ክፍለ ዘመን ብራናዎችን እና ሦስት መስቀሎችን የሚመልስ ሲሆን፣ ቀሪዎቹን ቅርሶች በሚቀጥሉት ከ5 እስከ 10 ዓመታት ውስጥ በሂደት ለመመለስ ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት ቅርሶችን በማስመለስ በኩል በመንግስት በኩል የታየው ቁርጠኛ የዲፕሎማሲ ብቃት የሚደነቅ መሆኑንም አንስተዋል።