ቀጥታ፡

243ኛው የማድሪድ ደርቢ

አዲስ አበባ፣  መስከረም 10 /2019(ኢዜአ)፡- በስፔን ላሊጋ የሰባተኛ ሳምንት መርሐ ግብር አትሌቲኮ ማድሪድ ከሪያል ማድሪድ ዛሬ የሚያደርጉት የደርቢ ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ጨዋታው ከቀኑ 11 ሰዓት ከ15 ከ70 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው በሜትሮፖሊታኖ ስታዲየም ይካሄዳል።

ባለሜዳው አትሌቲኮ ማድሪድ በ13 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሪያል ማድሪድ በ15 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

የማድሪድ ከተማ ክለቦቹ በሁሉም ውድድሮች ሲገናኙ የዛሬው ለ243ኛ ጊዜ ነው። ከዚህ በፊት ባደረጓቸው የእርስ በእርስ ጨዋታዎች ሪያል ማድሪድ 125 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል።

አትሌቲኮ ማድሪድ 60 ጊዜ አሸንፏል። 58 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

ሁለቱ ባላንጣ ክለቦች በላሊጋው እስከ አሁን 178 ጊዜ ተገናኝተው ሪያል ማድሪድ 92 ጊዜ አሸንፏል። አትሌቲኮ ማድሪድ 42 ጊዜ ሲያሸንፍ 44 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

አትሌቲኮ ማድሪድ ማሸነፍ ወደ ሊጉ መሪዎች ለመቅረብ ያስችለዋል።

የከተማ ተቀናቃኙ ሪያል ማድሪድ ማሸነፍ በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።

የ41 ዓመቱ ሚጉዌል አንጌል ኦርቲዝ አሪያስ ተጠባቂውን የደርቢ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

በተያያዘም ትናንት በተደረገ የሰባተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ባርሴሎና ሲቪያን 3  ለ 1 በማሸነፍ በ21 ነጥብ መሪነቱን አጠናክሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም