ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ተሰናበተ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ):-  የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ በታንዛንያ 4 ለ 0 ተሸንፏል።

ማምሻውን በኡሁሩ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ባሺሪ ኪባላ እና ጁማ ሳግዌ በተመሳሳይ ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል።

ታዳጊ ብሔራዊ ቡድኑ በተጋጣሚው ብልጫ ተወስዶበታል።

ውጤቱን ተከትሎ በአሜሪካዊው አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር የሚመራው ቡድን በምድብ አንድ በአንድ ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ከማጣሪያው ተሰናብቷል።

አዘጋጇ ታንዛንያ በስድስት ነጥብ ከምድቡ አንደኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ ወደ ግማሽ ፍጻሜ አልፋለች።

በምድብ ሁለት ዩጋንዳ፣ በምድብ ሶሶት ብሩንዲ ከየምድባቸው አንደኛ በመውጣት ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅለዋል።

በምድብ ሁለት ሱዳን በሶስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ምርጥ ሁለተኛ ሆና በማጠናቀቅ ግማሽ ፍጻሜ ገብታለች።

በዚሁ መሰረት አዘጋጇ ታንዛንያ ከብሩንዲ እና ዩጋንዳ ከሱዳን ማክሰኞ መስከረም 12 ቀን 2019 ዓ.ም የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ወደ ፍጻሜ የሚያልፉት ሁለት ሀገራት የሴካፋ ዞንን ወክለው እ.አ.አ በ2027 በጋና ለሚካሄደው ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማለፋቸውን ያረጋግጣሉ።

የሴካፋ ዞን ማጣሪያ መስከረም 15 ቀን 2019 ዓ.ም ይጠናቀቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም