በደራሲ እና የታሪክ ተመራማሪ ፍጹም ወልደማርያም የተጻፈው የዘመን አሻራ መጽሐፍ ለንባብ በቃ - ኢዜአ አማርኛ
በደራሲ እና የታሪክ ተመራማሪ ፍጹም ወልደማርያም የተጻፈው የዘመን አሻራ መጽሐፍ ለንባብ በቃ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ):-በደራሲ እና የታሪክ ተመራማሪ ፍጹም ወልደማርያም የተጻፈው የዘመን አሻራ መጽሐፍ ለንባብ በቅቷል፡፡
መጽሐፉ የ57 ኢትዮጵያውያንን እና የ3 የኢትዮጵያ ወዳጅ የውጭ ዜጎችን በድምሩ የ60 ታዋቂ ሰዎችን ታሪክ ሰንዶ የያዘ ሲሆን "60 ህይወቶች፣ 60 ታሪኮች እና አንድ የትውልድ አሻራ" በሚል መሪ ሃሳብ የተከተበ ነው።
መጽሐፉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ራስ መኮንን አዳራሽ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተመርቋል።
ከመጽሐፉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ቤተ-መጻሐፍትን ለማጠናከር እንደሚውልም በምረቃ መርሃ ግብሩ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዮሃንስ አድገህ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ደራሲው ሙሉ ጊዜውንና ገንዘቡን በመጠቀም ለትውልድ የሚተርፍ መጽሐፍ በማዘጋጀቱ ሊመሰገን ይገባል።
ከመጽሐፉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ለተቋሙ ማጠናከሪያ እንዲውል ማድረጉ አርአያ የሚሆን ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ተቋሙ የተቋቋመለትን ዓላማ ከዳር ለማድረስ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል።
የመጽሐፉ ደራሲ ፍጹም ወልደማርያም እንዳሉት፤ መጽሐፉ በተለያዩ የሙያ መስኮች ለሀገር አስተዋጽኦ ያበረከቱ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ዜጎችን መሰነዱን ጠቅሰዋል።
የታሪክ ምሁራን፣ የኪነ ጥበብና የሥነ ጥበብ ሰዎች፣ አርበኞችን ጨምሮ ትልልቅ ስብዕና የተላበሱ ሰዎች ታሪክ ረጅም ጊዜ የፈጀ ምርምር በማድረግ መጽሐፉ መዘጋጀቱን አብራርተዋል።
ለኢትዮጵያ አስተዋጽኦ ያበረከቱት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ ሲልቪያ ፓንክረስት እና ደጃዝማች ዑመር ሰመተር የህይወት ታሪክ በመጽሐፉ መካተቱንም ገልጸዋል።
መጽሐፉ ጥናትና ምርምር ለሚያከናውኑ ሰዎች በማጣቀሻነት የሚያገለግል መሆኑን ጠቁመው ታሪክን ማወቅ የሚፈልግ ማንኛውም ዜጋ ሊረዳው በሚችለው መልኩ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
የመጽሐፉ መዘጋጀት ትልልቅ አሻራ አኑረው ያለፉ ዜጎችን በመዘከር ቀጣዩ ትውልድ የራሱን ታሪክ እንዲጽፍ ለማነሳሳት ያለመ ነው ብለዋል።
ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በበኩሉ መጽሐፉ በህይወት ያሉትንም የሌሉትንም ታሪክ በሚገባ ሰንዶ የያዘ በመሆኑ ከባለታሪኮቹ ስንክሳር ለመማር ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቁሟል።
ደራሲና የታሪክ ተመራማሪ ፍጹም ወልደማሪያም በዚሁ ጊዜም ለኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ቤተ መጻሐፍት የሶፍት ኮፒና ሀርድ ኮፒ መጽሐፍትን ድጋፍ አድርጓል።