ቀጥታ፡

በክልሉ ተቋማት ላይ ተግባራዊ የተደረገው የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የተገልጋይን እርካታ እያረጋገጠ ነው

ባህር ዳር፤ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ):- በአማራ ክልል ተቋማት ላይ ተግባራዊ የተደረገው የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የተገልጋይን እርካታ እያረጋገጠ መሆኑ ተገለፀ።

በክልሉ በመጀመሪያው ዙር ወደ መንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የገቡ ስምንት ተቋማት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ተካሄዷል።


 

በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተሞች ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ሪፎርም አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሪፎርሙ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር የተገልጋይን እርካታ እያረጋገጠ መምጣቱን ገልጸዋል።

ይህም የመንግሥትን ተቋማት ነፃና ገለልተኛ እንዲሆኑ ከማድረግ ባሻገር የሠራተኛውን ችሎታና ብቃት ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በተቋማት በቴክኖሎጂ የታገዘ የዲጂታል አሠራርን እውን በማድረግ ፈጠራና ፍጥነት የታከለበት አገልግሎትን በፍትሐዊነት ተደራሽ መሆኑ ውጤት እያስገኘ ነው ያሉት።

በተለይም የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ፈጣንና ዘመናዊ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ማስቻሉን ጠቅሰው፤ በዚህም በስድስት ማዕከላት በተሰጠ አገልግሎት የተገልጋይ እርካታን 99 ነጥብ 7 በመቶ ማድረስ እንደተቻለም ገልጸዋል።


 

የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ባንችአምላክ ገብረማርያም በበኩላቸው፤ ሪፎርሙ የመንግሥትን አገልግሎትና አስተዳደር በውጤታማነት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በተለይም ከዚህ ቀደም በተቋማት ይስተዋሉ የነበሩ የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ወጪ ቆጣቢ በሆነ አግባብ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወን ማስቻሉን ጠቁመዋል።

ሪፎርሙ አሠራሮችን ዲጂታል በማድረግ ሥራን የማቅለልና የማዘመን ብሎም ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል መገንባትን ዓላማ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እስካሁን በተደረገ ጥረት ተቋማትን ለአሠራር ምቹ ከማድረግ ባለፈ የሕግ ማዕቀፎችን፣ ስትራቴጂዎችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን በማዘጋጀት ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

በክልል ደረጃ 69 ተቋማት 361 አገልግሎቶቻቸውን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ከ183 ሺህ 300 በላይ ደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።

በሪፎርሙ የግዥ፣ የንብረት አስተዳደርና የክፍያ ሥርዓትን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰው፤ የገቢ ሥርዓቱን ከማኑዋል ወደ ዲጂታል በማሳደግ ገቢ የመሰብሰብ አቅም ከፍ እንዲል ማድረጉን አብራርተዋል።

ትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና፣ ፕላንና ልማት እና ሥራና ክህሎት ቢሮዎች ሪፎርሙን በመተግበር የተሻለ ሥራ ማከናወናቸውን ተናግረዋል።

የተገኙ ውጤቶችን በማጠናከርም በየደረጃው የተሻለ ግንዛቤ ተፈጥሮ ወደ ተሟላ አፈጻጸም ለመግባት በቅንጅት መረባረብ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በመድረኩ በሪፎርሙ ወደ ተግባር የገቡ ተቋማት አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን የየተቋማቱ የሪፎርም አፈጻጸም ግምገማ ተካሄዷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም