የዓለም አቀፍ ዲጂታል ሽግግር ፈጣን አብዮት፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የልህቀት ማዕከል ፍኖት!! - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም አቀፍ ዲጂታል ሽግግር ፈጣን አብዮት፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የልህቀት ማዕከል ፍኖት!!
በታዬ ለማ
ዓለም ከኢንዱስትሪ አብዮት ወደ ዲጂታል፣ ከዲጂታል አብዮት ደግሞ ወደ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የተጓዘችበት ፈጣን ሽግግር የሰውን ልጅ የኑሮ፣ ሥራና የሀሳብ ምኅዳር እየቀየረ ይገኛል። ዛሬ ላይ ቴክኖሎጂ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚደግፍ አንድ ዘርፍ ብቻ አይደለም፤ የምርታማነት፣ የፈጠራ፣ የውድድርና የሀገራዊ አቅም መሠረት እየሆነ መጥቷል።
በተለይም የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ሽግግር አዲሱ የዕድገት ሞተር ሲሆን የጤና፣ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ዲጂታል ግብይት፣ ትምህርትና የመንግሥት አገልግሎቶችን መደገፍ ከጀመረ ሰነባብቷል። ስለዚህ የወቅቱ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ውድድር በተሻለ የሰው ኃይል፣ የቴክኖሎጂ ነፃነት እንዲሁም ከሀገር ውስጥ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እውነት ጋር የተጣጣመ ትግበራን ማዕከል ያደረገ ሆኗል።
ይህ የዓለም አቀፍ ሽግግር ለአፍሪካ በርካታ ዕድሎችን ይዞ መጥቷል። አህጉሪቱ በአንድ በኩል የዲጂታል መሠረተ ልማት፣ የኤሌክትሪክና የኢንተርኔት ተደራሽነት፣ የዳታ አቅምና የሰው ኃይል ክፍተቶች አሏት። በሌላ በኩል ወጣት የሰው ኃይል፣ ታዳጊ የቴክኖሎጂ ገበያና በብዙ ዘርፎች አሁንም ያልተሟሉ ፍላጎቶች ስላሏት የፈጠራ ዕድልን ያበረታታል።
ይህንን እውነት የተገነዘበው የአፍሪካ ሕብረት በ2024 የአህጉራዊ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ስትራቴጂን ቀርጿል። ስትራቴጂውም የሰው ሠራሽ አስተውሎትን (AI) በአፍሪካ የልማትና የሕዝቦቿ ፍላጎት እንዲሁም በአህጉሪቷ እውነታ ላይ የተመሠረተ ሆኖ እንድትጠቀምበት የሚያበረታታ ነው።
በዚህም አፍሪካ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ተጠቃሚ ብቻ ሳትሆን በዳታ፣ በምርምር፣ በሶፍትዌር፣ በሰው ኃይልና በአፍሪካዊ መፍትሔዎች ላይ የራሷን አቅም የምትገነባበትን ዕድል ይፈጥራል። በ2025 በአዲስ አበባ በተካሄደው የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ልማትና ቁጥጥር ከፍተኛ ደረጃ ውይይት ላይ የአፍሪካ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ስትራቴጂክ ልማት የዲጂታል መሠረተ ልማት፣ የዳታ ጥራት፣ የክህሎትና ምርምር አቅምን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ተሰጥቷል።
ኢትዮጵያ፤ ከዲጂታል 2025 ወደ ዲጂታል 2030
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍና የአፍሪካን ፈጣን የዲጂታል ሽግግር በመገንዘብ የዲጂታል ዘርፍ የብዝኅ ኢኮኖሚ ልማት አካል በማድረግ መጓዝ ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል። የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ዋና ትኩረቱን የዲጂታል ምኅዳር ግንባታ፣ የዲጂታል መሠረተ ልማት ማስፋፋት፣ የዲጂታል ክፍያንና የመንግሥት ዲጂታል አገልግሎትን ማጠናከር ማዕከል በማድረግ በሁሉም ዘርፍ የታለመለትን ዓላማ በማሳካት ወደ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ተሸጋግሯል።
ይህ ሽግግር ከአንድ ስትራቴጂ ወደ ሌላ የሚደረግ የስያሜ ለውጥ ብቻ አይደለም። ከዲጂታል መሠረተ ልማት ግንባታ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ጥልቀት የሚደረግ ሽግግር እንጂ። ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂም የዲጂታል መሠረተ ልማት ማስፋፋትን፣ የመረጃ አስተዳደርን፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎትን (AI) እና የዲጂታል አገልግሎት ተደራሽነትን በቁልፍ ግብ ይዟል። በዚህም በሁሉም ዘርፍ ተጨባጭ ውጤቶች ማስገኘቱን ቀጥሏል።
የዲጂታል መሠረተ ልማት ግንባታ፤ የኢትዮጵያ ሽግግር አስቻይ ምኅዳር!!
የዲጂታል አቅም በመተግበሪያና ሶፍትዌር ልማት ብቻ የሚገነባ አይደለም። የኃይል፣ ኢንተርኔት፣ ዳታ ማዕከላት፣ የቴሌኮሙኒኬሽንና የሳይበር ደኅንነት መሠረተ ልማቶች ግንባታም መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው። በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የተፋጠነው የግንኙነት መሠረተ ልማት እመርታ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን በጽኑ መሠረት አንጾ አልፏል።
ለአብነትም በፈረንጆቹ 2025 መጨረሻ 97 ሚሊዮን የሞባይል ተመዝጋቢዎች፣ 57 ሚሊዮን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችና 1 ሺህ 30 ከተሞች የ4G የኢንተርኔት መሠረተ ልማት ተጠቃሚ ሆነዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል፤ የመንግሥት አገልግሎት ወደ ዜጎች በር እና የእጅ ስልክ
የዲጂታል ሽግግር የመጨረሻ ትርጉም ዜጎች በሚያገኙት አስቻይ የአገልግሎት ምኅዳር ላይ ይመዘናል። በዚህም የመሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት ከተለያዩ ተቋማት የሚገኙ አገልግሎቶችን በአንድ የዲጂታል ምኅዳር ለማቀናጀት የሚያግዝ እርምጃ ሆኖ ከመጣ ሰነባብቷል።
ይህ ዲጂታል ምኅዳር የመንግሥት ተቋማት አገልግሎቶች በአንድ ላይ በማቀናጀት ዜጎች ያለ እንግልት በቀላሉ የተቀላጠፈ አገልግሎት የሚያገኙበትን ዕድል ፈጥሯል። የዲጂታል ሽግግሩ ዋና ዓላማ የሕዝብን እርካታ ማረጋገጥ ነው። በዚህም የመሶብ መርሃ ግብር በአካል በመሶብ የአንድ ማዕከላት፣ በጋዝና ኤሌክትሪክ በሚሠሩ መኪኖች በተንቀሳቃሽና የተቀናጀ አገልግሎት በሞባይል መተግበሪያ የመንግሥት አገልግሎቶች ለሕዝብ ቅርብ ሆነዋል።
ይህም የሕዝብን እንግልት በማስቀረት የመንግሥት አሠራር ግልጽነትንና መልካም አስተዳደርን በማስፈን በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ተጨባጭ ለውጥ እመጣ ይገኛል። በዚህም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ በዲጂታላይዜሽን፣ በፋይዳቨርስና ኢትዮ-ኮደርስ በሕዝብና መንግሥት መካከል መተማመንን በማጎልበት በሰው ሠራሽ አስተውሎት ልማት መስክ አስቻይ የፈጠራና ክህሎት ምኅዳር እየፈጠረ ይገኛል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI)፤ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል መፍትሔን የማፍለቅ ህልም
ዓለም በዲጂታል ሽግግር አዲስ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። በተለይም ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ከቴክኖሎጂ ዘርፍ አልፎ በኢኮኖሚ፣ በጤና፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በፋይናንስና በመንግሥት አገልግሎት የአሠራር ሥርዓቶችን በማቀላጠፍና በማዘመን ጉልህ ሚና እየተወጣ ነው።
አፍሪካም ከዓለም አቀፍ የውድድር ምኅዳር ውጭ አይደለችም። ይህም ከአህጉሪቷ ፍላጎትና ነባራዊ እውነታ ጋር የተቆራኘ የሰው ሠራሽ አስተውሎት መፍትሔን ማፍለቅ እንደሚያስፈልግ የሚጠይቅ አዲስ ምዕራፍ ነው። ኢትዮጵያም የዲጂታል ሽግግርን ከአገራዊ የልማት ግቦቿ ጋር በማስተሳሰር በእመርታዊ ለውጥ እየተጓዘች ይገኛል። ለዚህም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ሁነኛ መሠረትን ጥሏል።
የኢትዮጵያ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ጉዞም በዲጂታል 2025 የተጣለውን መሠረት ወደ ዲጂታል 2030 በማሸጋገር ጭምር ፈጠራና ክህሎትን የሚያበለጽግ ምኅዳርን ፈጥሯል። ይህም የዲጂታል 2030 ራዕይና የሰው ሠራሽ አስተውሎት ልማት (AI) በአንድ ሰንሰለት የሚገነቡበትን አዲስ የቴክኖሎጂ ምዕራፍ ከፍቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ሕብረት የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ (Champion) ሆነው መሾማቸው ኢትዮጵያ እየሄደችበት ያለውን ስኬት አሳይቷል።
የመደመር አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ፤ የኢትዮጵያ አዲስ አህጉራዊ የልህቀት ማዕከልነት ራዕይ
የመደመር አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁ ተሰይሞ ወደ ሥራ የሚገባ የይስሙላ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም አይደለም። ኢትዮጵያ በአፍሪካ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) የምርምር፣ ክህሎትና የፈጠራ ማዕከል በማድረግ የመጪው ዘመን ፍኖት የሚያበስር ተቋም ነው።
ተቋሙም ከኢትዮጵያ ባሻገር በአፍሪካውያን ቋንቋዎችና የማኅበረሰብ ዕውቀቶች ላይ የተመሠረተ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI)፣ ሀገር በቀል መፍትሔ አመንጪ ምርምሮች፣ የዲጂታል ትስስርና ፈጠራን የሚያበረታታ ወሳኝ የመጪው ዘመን የተስፋ ብርሃንን ያነገበ ነው።
ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕንድ ኒው ዴልሂ በተካሄደው 18ኛው የብሪክስ ጉባኤ፤ ኢትዮጵያ ለሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ በሰጠችው ትኩረት የመደመር አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ እንዲወለድ ያደረገ ነው።
የአፍሪካን አህጉር በይበልጥ የሚያግዙ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥርዓቶችን በማበልጸግ ኢትዮጵያን አህጉራዊ የዘርፉ የልህቀት ማዕከል የሚያደርጋት ነው። ለዚህም ከብሪክስ አባል ሀገራት የትምህርት፣ የቴክኖሎጂ እና የምርምር ተቋማት ጋር ጠንካራ ትብብር ለመፍጠር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ጉዞ መነሻውን ከሀገራዊ የዲጂታል ሽግግር አጀንዳ በማድረግ ወደ አህጉራዊ የቴክኖሎጂ ትብብር የሚሸጋገር ተስፋን የሰነቀ ነው። የመደመር አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲም የዚህ ጉዞ ተቋማዊ መገለጫ ሆኗል። ይህም ኢትዮጵያ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) የቴክኖሎጂ ፈጠራ ተጠቃሚ ብቻ ሳትሆን ለአፍሪካ እውነታ የሚመጥኑ መፍትሔዎችን የምታመነጭ የምርምርና የፈጠራ ማዕከል የመሆን ራዕይ የሚያጠናክር ይሆናል፡፡