ቀጥታ፡

በክልሉ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ተቋራጮች ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት በመጨረስ እድገቱን ማፋጠን አለባቸው

ባህር ዳር፤ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ተቋራጮች ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት በመጨረስ ሁለንተናዊ እድገቱን በማፋጠን የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተጠቆመ።

የአማራ ክልል ኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማህበር 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን በባህር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።


 

በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ከተሞች ክላስተር አስተባባሪ አሕመዲን መሀመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ የመደመር መንግሥት ፕሮጀክቶችን ፈጥኖ በመጀመርና በጥራት በመጨረስ ጠንካራ እሴቶችን ገንብቷል።

በዚህም ከተለመደው አካሄድ በመውጣት በፈጠራ፣ በፍጥነት፣ በጥራትና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ አሰራርን ተግባራዊ ማድረጉን አስረድተዋል።

የኮንስትራክሽን ዘርፉ ከነበረበት የዘመናት ውድቀት በማንሰራራት የክልሉ የአምስት ዓመት ስትራቴጂና የ25 ዓመቱ የአሻጋሪና የእድገት ፍኖተ ካርታ ግብን ለማሳካት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ መምጣቱን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት በመጨረስ ለሀገር እድገትና ለህዝብ ተጠቃሚነት ለማዋል በዘርፉ የተሰማሩ ተቋራጮች ትልቅ ሚና እንዳላቸው አረጋግጠዋል።

በፕሮጀክት አስተዳደር ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በመሙላት ክልሉንም ሆነ ሀገርን በትክክለኛው የእድገት አቅጣጫ እንድትጓዝ መንግሥትና ተቋራጮች በጋራ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኮንስትራክሽን ማህበር አባላቱ አቅም ካላቸው የሀገር ውስጥና የአለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ትስስር በመፍጠር መንግሥትና ህዝብ የጣለባቸውን ሚና እንዲወጡም አስፈላጊው እገዛ እንደሚደረግ አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉቀን ቢተው በበኩለቸው ማሕበሩ ፍትሃዊ የስራ ውድድር እንዲሰፍን እና ህጋዊና ስርዓት ያለው ግብይት እንዲተገበርና የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

ማህበሩ የስነ- ምግባር ችግሮችን በማረም ዘርፉ ለሀገሪቱ እድገት ያለውን ከፍተኛ ሚና እንዲወጣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መስራቱን እንደሚቀጥል ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም