"ዮ ማስቃላ"--ከእንጊጫ እስከ ጮዬ - ኢዜአ አማርኛ
"ዮ ማስቃላ"--ከእንጊጫ እስከ ጮዬ
(በሳሙኤል አየነው -ከኢዜአ አርባምንጭ ቅርንጫፍ)
የጋሞ ማህበረሰብ የራሱ የሆነ የዘመን አቆጣጠር፣ ባህልና ቋንቋ አለው። ከእነዚህም የሰላም፣ የአብሮነትና የይቅርታ እሴትን አቅፎ የያዘው የዘመን መለወጫ በዓል "ዮ ማስቃላ" በቀዳሚነት ሊጠቀስ የሚችል ሲሆን በትውልድ ቅብብሎሽ ሲወርድ ሲዋረድ እየተከበረ ዛሬ ላይ ደርሷል።
ማህበረሰቡ ዘመን ተሻጋሪ የጋራ እሴት ያለው ጠንካራ ባህል የገነባ በመሆኑ በአብሮነት፣ በሰላም፣ በአንድነት፣ በፍቅርና በይቅርታ ተቻችሎና ተከባብሮ ዘመናትን ተሻግሯል። አሁንም ይህንኑ እሴቱን በማጠናከር ቀጥሏል።
ከጋሞዎች የዘመን መለወጫ በዓል ''ዮ ማስቃላ'' እሴቶችና ሌሎች ጉዳዮችን መሰረት በማድረግ ኢዜአ ከዞኑ ባህልና ስፖርት መምሪያ የባህል እና ታሪክ ጥናት ልማት ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ወንድይፍራው ከተማ ጋር ቆይታ አድርጓል።
አስተባባሪው እንደገለጹት፤ ጋሞዎች የዘመን መለወጫ በዓላቸው ''ዮ ማስቃላ'' ከመከበሩ አስቀድሞ አባቶች ለእርድ ከብት፣ ለአልባሳትና ጌጣጌጥ መግዣ እናቶች ደግሞ ለባህላዊ ምግብና መጠጥ እንዲሁም ቅመማ ቅመም የሚሆን የገንዘብ ቁጠባ ያደርጋሉ። ጋሞዎች ቁጠባን የለመዱት ከጥንት አባቶች በተረከቡት የዘመን መለወጫ ቅርስ ጀምሮ ሲሆን ዛሬ ላይ ኑሮን ለማሸነፍ ቁጠባ በሁሉም አካባቢ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።
የበዓሉ ዝግጅት ምዕራፍ በአካባቢው አጠራር "እንጊጫ" ይባላል፤ በዓሉ ሲቃረብ በተቆጠበው ገንዘብ በመስከረም ወር ከመጀመሪያው ሣምንት ጀምሮ አባወራዎችና እማወራዎች በየገበያው የተለያዩ የበዓል ቁሳቁሶችንና የፍጆታ ዕቃዎችን መሸመት ይጀምራሉ። በዚህም ወቅት አባወራው ለበዓሉ የሚሆን ሠንጋ፣ ለመላው ቤተሰብ አልባሳት እና ለእማወራዋ ጌጣጌጥ የማቅረብ ኃላፊነቱን ሲወጣ፤ በአንጻሩ እማወራዋ ቅቤ፣ ለቅመማ ቅመምና ለባህላዊ ምግቦች እና መጠጦች ትኩረት በመስጠት ዝግጅት ታደርጋለች።
በበዓሉ ጅማሮ እንደየ አመቺነቱ ሁሉም ከቤተዘመድና ከጎረቤት ጋር በመሆን አማካይ በሆነ ስፍራ ከብቶችን የሚያርዱ ሲሆን፤ በስፍራው ከየሥጋው ዓይነት ያዘጋጁትን ከቀማመሱ እና በቦርዴ ካወራረዱ በኋላ የድርሻቸውን ሥጋ ይዘው ወደ የቤታቸው በማቅናት ቁርጥ እና ጎረድ ጎረድ ጥብስ ሥጋ በቅቤ ተለውሶ በትልቅ ወጭት ላይ ቀርቦ ይመገባሉ። ከባህላዊ ምግቦች መካከል የገብስ ቅንጬ፣ የቡላ ቆጮ እና ከገብስ የሚዘጋጅ ቂጣ፣ የቡላ ፍርፍር፣ ሐረግ ቦዬ ሲሆኑ፤ ከመጠጥ ደግሞ ቦርዴ፣ የማርና የቦርዴ ውህድ የመሳሰሉ ባህላዊ መጠጦችም በስፋት ይቀርባሉ።
"ዮ ማስቃላ" ለሰላም እሴት ግንባታ የራሱ የሆነ ጉልህ ፋይዳ አለው፤ በጋሞዎች ዘንድ አዲሱን ዓመት ቂም፣ ቁርሾ እና ሐዘን ይዞ መሻገር ነውር በመሆኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች የተጣሉት ይታረቃሉ፤ ይቅር ይባባላሉ፤ ያዘኑት ደግሞ ሐዘናቸውን በመተው በአዲስ መንፈስ ይጽናናሉ። በተለያዩ ስፍራዎች ተራርቀው በናፍቆት የቆዩ ዘመድ አዝማድ እና ወዳጆች ተሰባስበው በዓሉን በጋራ ማክበር የ"ዮ ማስቃላ" ሌላኛው የመደመር፣ የአብሮነትና የአንድነት ገጽታ ነው።
"ዮ ማስቃላ" ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ለእንስሳትም የደስታና የጥጋብ ጊዜ ተብሎ የሚታሰብ በመሆኑ የቤት እንስሳትን ቀደም ሲል ተከልለው በለሙ የግጦሽ ስፍራዎች እንዲሰማሩ በማድረግ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በአንድ ልብ ፊታቸውን ወደ በዓሉ ያዞራሉ።
ከጋሞ ሀገር ሽማግሌዎች መካከል አስተያየታቸውን የሰጡት አሜሌ አልቶ፤ የመስቀል ዳመራ ችቦ ሥርዓት፣ የአባቶች ምርቃት እና ባህላዊ ጨዋታዎች እንዲሁም አብሮ መብላትና መጠጣት ከ"ዮ ማስቃላ" ዘመን መለወጫ በዓል አበይት ኩነቶች እንደሚጠቀሱ አጫውተውናል።
ችቦ የሚወጣበት ሰዓት ሲደርስ አባት የራሱን ችቦ ለኩሶ የቅቤ ምንቸቱን፣ የቤቱን ምሰሶ፣ የከብቶቹን በረት እና የበር ጉበኖችን ግራ እና ቀኝ በችቦው ጫፍ በማነካካት ቀጥታ ወደ ደመራ ሥርዓት እንደሚያመሩ ጋሽ አሜሌ አንስተዋል። በዚህም ወቅት ወንድ ልጆች የየራሳቸውን ችቦ ተራ በተራ እየለኮሱ አባታቸውን ተከትለው "ዮ..ዮ..ማስቃላ" እያሉ በመጨፈር ወደ ደመራው ቦታ ከደረሱ በኋላ አባት በቀዳሚነት፣ ልጆች ደግሞ በተከታይነት ደመራውን ይለኩሳሉ።
በ"ዮ ማስቃላ" ከታቀፉ እሴቶች መካከል የመደጋገፍ፣ አብሮ የመብላት፣ አብሮ የመጠጣትና አብሮ የመጨፈር አንዱ ሲሆን፤ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖች በዓሉን ለማክበር አይጨነቁም። ምክንያቱም ለበዓሉ የተዘጋጀው ምግብና መጠጥ ደሃ፣ ሀብታም ሳይባል ካለምንም ልዩነት ያላቸው ከሌላቸው ጋር ተጠራርተው በአብሮነት የሚደሰቱበት ልዩ ጊዜ ነው። በዓሉ ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለእንስሳት እና ለአእዋፋትም ጭምር የደስታ ጊዜ ተብሎ የሚታመን በመሆኑ በወቅቱ ምግብ ከሰው አልፎ ለእንስሳት እና ለአእዋፋትም ይትረፈረፋል።
አዲስ ዓመት እንደመሆኑ ሁሉም የቤተሰብ አባላት በአዲስ አልባሳት የሚያሸበርቁ ሲሆን፤ እናት ደግሞ በጌጣጌጥም ደምቃ የቤቱ ንግስት መሆኗን ታሳያለች። በ"ዮ ማስቃላ" ጊዜ ተጋቢ ጥንዶች በይፋ ማኅበራዊ ዕውቅና የሚያገኙበት ልዩ አጋጣሚ መሆኑንም ጋሽ ዓመሌ ይናገራሉ። የአንቱታን ክብር የሚጎናጸፉት በአልባሳትና ጌጣጌጥ ተውበው ከቤተሰብ፣ ሚዜዎችና አጃቢዎች ጋር ገበያ ወጥተው ራሳቸውን ካሳዩ በኋላ ነው።
በተጨማሪም ማኅበራዊ ግዴታዎችን ለመወጣትም ሆነ ለኃላፊነት የሚታጩት ያን ሥርዓት ከፈጸሙ በኋላ ሲሆን፤ በዚህም ጊዜ እንስቷ ማህፀኗ ጽንስ መሸከም እንዲችል በሚል ለወራት ተቀልባና ታርሳ ትወጣለች፤ ይህ በአካባቢው ቋንቋ የ"ሶፌ" ሥርዓት ይባላል። የማኅበረሰቡ የጋራ የሆኑ የሰላም፣ የእርቅና የአብሮነት እሴቶች ደግሞ የማኅበረሰቡን አንድነት ከማጽናት ባለፈ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የማይነጥፍ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።
እንደ "ዮ ማስቃላ" ያሉ የሕዝብና የሀገር አንድነትን የሚያጸኑ የአደባባይ በዓላት ሳይበረዙና ሳይከለሱ ለትውልድ ተጠብቀው እንዲቆዩ የመንግሥት አካላት፣ ምሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች እየተወጡ ያለውን ሚና በማጠናከር የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
ጋሞዎች "ዮ ማስቃላ"ን በወርሃ መስከረም ብቻ አክብረው የሚያበቁ ሳይሆን ከዕለት ተዕለት የኑሮ እንቅስቀሴን ጎን ለጎን የበዓሉ ድባብ ሳይደበዝዝ እስከ ታህሳስ ወር መገባደጃ በማክበር፣ በመጨረሻም የሽኝት (ጮዬ ማስቃላ) በየስፍራው ተዘጋጅቶ ከተገባበዙ በኋላ በአባቶች ተመራርቀው ይለያያሉ።
"ዮ ማስቃላ" የአብሮነትና የአንድነት እንዲሁም ሰርቶ የመለወጥ የተስፋና የብርሃን ምልክትና ካስማ ተደርጎ የሚወሰድ በርካታ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እሴቶችን በውስጡ የያዘ ሀብት ነው። የዘንድሮ የ"ዮ ማስቃላ" በዓል በመስከረም 11 እና 12/2019 ዓ/ም በተለያዩ መርሃ ግብሮች በድምቀት ይከበራል።