በቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚሰጡ ስልጠናዎች ለስራ ፈጠራ እንዲያግዙ የማድረጉ ተግባር ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
በቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚሰጡ ስልጠናዎች ለስራ ፈጠራ እንዲያግዙ የማድረጉ ተግባር ይጠናከራል
ሆሳዕና፤ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ) ፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የሚሰጡ ስልጠናዎች ዜጎችን ወደ ስራ ፈጠራ የሚያሸጋግሩ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ገለፀ።
የሆሳዕና ፖሊ ቴክኒክን ጨምሮ በክላስተሩ የሚገኙ ሰባት የፖሊ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጆች በተለያዩ መስኮች ያሰለጠኗቸውን ከ1 ሺህ 190 በላይ ተማሪዎችን አስመርቀዋል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊና የስልጠና ተቋማት አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ኢንጂነር ሰለሞን ፈርሻ እንዳሉት፤ በክልሉ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት የሚሰጡ ሥልጠናዎች ዜጎችን ክህሎትና እውቀትን በማስጨበጥ ከሥራ ጠባቂነት ወደ ሥራ ፈጣሪነት የሚያሸጋግሩ ናቸው።
ቢሮው ዲጂታል ቴክኖሎጂን ጨምሮ የአካባቢን ጸጋ ማዕከል ያደረጉ አጫጭር ሥልጠናዎችን በመስጠት ብቁ፣ ተወዳዳሪና ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ለማስቻል በዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም የማኅበረሰቡን ችግር መሠረት ያደረጉ የፈጠራ ሥራዎችን በማፍለቅና በማሸጋገር ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ የተገኙ ውጤቶችንም የማሳደግ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ምሩቃኑ በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲጠቀሙበት አስገንዝበዋል።
የሆሳዕና ፖሊ ቴክኒክ ዲንና የክላስተር ኮሌጆች አስተባባሪ አቶ አዎል ሸንጎ በበኩላቸው፤ ኮሌጁ የገበያ ፍላጎትንና የአካባቢን ጸጋ መሠረት ያደረጉ ሥልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም ብቁና ሥራ ፈጣሪ ተወዳዳሪ ዜጎችን ከማፍራቱም በተጨማሪ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፉ የፈጠራ ሥራዎችን በማፍለቅ የኢንተርፕራይዞችን አቅም በመደገፍ ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በክላስተሩ በመደበኛና በተከታታይ መርሐ ግብር ሥልጠናቸውን በአግባቡ ያጠናቀቁ 1 ሺህ 190 ሰልጣኞች ዛሬ ተመርቀዋል።
የሆሳዕና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ከአውቶሞቲቭ ትምህርት ክፍል ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው ረታ ተከተል እንደገለጸው፤ በትምህርት ቆይታው ያገኘውን እውቀት ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችለውን በቂ ክህሎት ማግኘቱን ተናግሯል።
ሌላዋ ተመራቂ ሊንቲሴ ዳዊት በበኩሏ የተመረቀችበት የሆቴል ማኔጅመንትና ቱሪዝም ዘርፍ በመንግሥት ልዩ ትኩረት የተሰጠውን የቱሪዝም ዘርፍ ይበልጥ ለማነቃቃት የሚያስችል መሆኑን ገልጻለች።
በተለይም በዘርፉ ያሉትን አማራጮች ተጠቅማ ሥራ በመፍጠር ተጠቃሚነቷን ለማሳደግ እንደምትተጋም ነው የገለጸችው።
በመርሐ ግብሩ የክልል፣ የኮሌጁ፣ የሃዲያ ዞን ከፍተኛ አመራሮችና የተመራቂ ተማሪ ቤተሰቦች ታዳሚ ሆነዋል።