በአማራ ክልል የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በተለያዩ መስኮች ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በተለያዩ መስኮች ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ ነው
ባህርዳር፤ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ)፦ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በክልሉ በተለያዩ መስኮች ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ እንድሪስ አብዱ ገለጹ።
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎችም የስራ ኃላፊዎች በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙ የተለያዩ የኢንዱስትሪ ልማት እንቅስቃሴዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት ማብራሪያ የሰጡት የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ እንድሪስ አብዱ፤ በክልሉ የተፈጠረው አስቻይ ሁኔታ የኢንቨስተሮችን ተሳትፎ እያጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።
በ2018 በጀት ዓመት ብቻ ከ553 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት ያስመዘገቡ በክልሉ የተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት መግባታቸውን ጠቁመዋል።
በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር መቻሉ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ አስችሏል ያሉት ኃላፊው በዚህም ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።
በዚህም የክልሉ የአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነት እና የኢንዱስትሪ ዘርፍ እድገት እያሳየ የመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ኢንቨስት የሚያደርጉ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ ስለመምጣቱም ጠቁመዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም በዘርፉ የሚሰማሩ ኢንቨስተሮችን የመሳብ፣ የዘርፉን እድገትና ምርታማነትን የማስቀጠል ስራ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር ጉብኝትም ዋነኛ ዓላማ የኢንዱስትሪዎችን የስራ እንቅስቃሴ በመመልከት ለማበረታታት እና ለችግሮችም የመፍትሄ አቅጣጫ ለማመላከት መሆኑን ገልጸው በዚሁ መሰረት ቀጣይነት ያለው ስራ ይከናወናል ብለዋል።