በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአርሶ አደሩ በመስኖ የማልማት አቅም እየተገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአርሶ አደሩ በመስኖ የማልማት አቅም እየተገነባ ነው
ጂንካ፤ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርሶ አደሩን ከዝናብ በተጨማሪ በመስኖ ዓመቱን ሙሉ የማምረት አቅም እየተገነባ መሆኑን የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ገለጸ።
በክልሉ በአሪ ዞን ሰሜን አሪ ወረዳ ከ58 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለመስኖ አገልግሎት የተጠለፈው ''የሳላ'' ወንዝ ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
የመስኖ ፕሮጀክቱ ከ80 ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከሁለት መቶ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል።
በወቅቱም የቢሮው ኃላፊ አቶ ኤካል ነትር እንዳሉት፣ የአካባቢውን አርሶ አደሮች ከክረምት ዝናብ በተጨማሪ በበጋ መስኖ ለማልማት የሚያስችላቸው ዕድል ተፈጥሯል።
የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እና የኢኮኖሚ አቅሙን ለማሳደግ የመስኖ አውታሮችን የማስፋፋት ሥራ የክልሉ መንግሥት በትኩረት እየሠራ መሆኑን አንስተዋል።
በሣላ ወንዝ የተሠራው አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክት አርሶ አደሩን ከክረምት ዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ የሚደረገው ጥረት አካል መሆኑን ገልጸው በዚህም የአርሶ አደሩን በመስኖ የማልማት አቅም እየተገነባ መሆኑን አስረድተዋል።
ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የመስኖ ፕሮጀክት የአካባቢው አርሶ አደሮች በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥና የገቢ አቅማቸውን ለማሳደግ እንደሚረዳ ተናግረዋል።
የሣላ የመስኖ ፕሮጀክት በሥርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም የተገነባ ሲሆን፣ ከ80 ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከሁለት መቶ በላይ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸውን በቀጥታ ተጠቃሚ ያደርጋል ነው ያሉት።
የሰሜን አሪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ጎሳዬ ጉሳሬ በበኩላቸው፣ በወረዳው የሳላ ወንዝ መስኖ ፕሮጀክትን ጨምሮ ሌሎች የመስኖ ልማት ስራዎችን በማዘመንና ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የአርሶ አደሩ ሕይወት እየተለወጠ ነው ብለዋል።
የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ አፌዶ ወርቁ በበኩላቸው፣ መንግሥት የአርሶና የአርብቶ አደሩን ሕይወት በዘላቂነት ለመለወጥ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
አርሶ አደሮቹ መንግሥት በፈጠረላቸው ዕድል በመጠቀም ኑሯቸውን ለመለወጥ መትጋት እንዳለባቸው አሳስበው፤ የመስኖ አውታሩ በደለል እንዳይሞላ መጠበቅና መንከባከብ እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
ከአካባቢው አርሶ አደሮች መካከል አቶ ንጋቱ ፀጋዬ እና አቶ ፌታ ጊዲፎ፣ የሳላ ወንዝ መስኖ ፕሮጀክት ለአርሶ አደሩ ዓመቱን ሙሉ በምርት ሥራ ላይ ተሰማርተው እንዲቆዩ ትልቅ ዕድልን እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
ቀደም ሲል የግብርና ሥራዎቻቸው በዝናብ ላይ ብቻ ጥገኛ በመሆኑ ውስን ሰብሎችን ብቻ በማልማት ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ይመሩ እንደነበር ጠቅሰው፣ አሁን በአካባቢው ለመስኖ አገልግሎት የሚውል ወንዝ በመጠለፉ ዓመቱን ሙሉ ማልማት የሚችሉበት አቅም መፈጠሩን ገልጸዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ እና የአሪ ዞን የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች እና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።