ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለሰ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው

ደሴ፤ መስከረም 9/2019(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል ኢኮኖሚው በሚያመነጨው ልክ ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በቅንጅት የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ ።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች መምሪያ የገቢ አሰባሰብ አቅሙን በማሳደግ ህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የምክክር መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል።


በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፍቅረማሪያም ደጀኔ እንደገለጹት፤ የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የገቢ አቅምን አሟጦ ለመጠቀም የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ። 

በተለይም ክልሉ የሚያመነጨውን ገቢ በሚፈለገው ልክ በመሰብሰብ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰፋፊ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ግብ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን ዲጂታል በማድረግና አዳዲስ አሰራሮችን በመከተል በተያዘው በጀት ዓመት ከ166 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ነው የጠቆሙት።

እስካሁን በተደረገው ጥረት ከ18 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉንም አስታውቀዋል። 


 

ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ6 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው ሲሆን፤ በክልሉ እያደገ የመጣውን ገቢ የመሰብሰብ አቅም በማስቀጠል የተሻሉ ሥራዎችን ለማከናወን መታቀዱንም አክለው ገልጸዋል።

በክልል ኢኮኖሚው የሚያመነጨው ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ ህብረተሰቡ የሚያነሳችውን የልማት ጥያቄዎች በሚፈለገው ልክ ለመመለስ በቅንጅት የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፤ በተያዘው በጀት ዓመት ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ የተሻሉ ተግባራትን ለማከናወን ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።


 

በከተማዋ በበጀት ዓመቱ 8.2 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን፤ አዳዲስ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን በመተግበር እቅዱን ለማሳካት ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የደሴ ከተማ ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ መንግስቱ አበበ በበኩላቸው፤ በከተማዋ በበጀት ዓመቱ የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴም ከ719 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አመልክተው፤ መምሪያው የገቢ አሰባሰብ አቅሙን በማሳደግ የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በዚሁ የምክክር መድረክ ላይ የክልል፣ የከተማና የክፍለ ከተማ አመራሮች እንዲሁም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም