ግብፅ ከፍተኛ የውሃ ሀብት እያላት ደካማ የውሃ አስተዳደር የምትከተል ሀገር ናት - አቶ ጌታቸው ረዳ - ኢዜአ አማርኛ
ግብፅ ከፍተኛ የውሃ ሀብት እያላት ደካማ የውሃ አስተዳደር የምትከተል ሀገር ናት - አቶ ጌታቸው ረዳ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ):- ግብፅ ከፍተኛ የውሃ ሀብት እያላት ደካማ የውሃ አስተዳደር የምትከተል ሀገር መሆኗን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ ገለጹ።
አቶ ጌታቸው ረዳ ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ግብፅ የዓባይ ወንዝን የራሷ ብቻ አድርጎ የመመልከት ኋላ ቀር አካሄድ እንደምትከተል ተናግረዋል።
የግብፅ አቋም የወንዙን እውነተኛ ምንጭ ጨምሮ ፍጹም ሐቅን የሚክድ የድፍረት አካሄድ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ደግሞ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
ግብፅ ሳይንስን በተቃረነ መልኩ በዓባይ አጠቃቀም ዙሪያ የምታራምደው የተሳሳተ አካሄድ ግብፃዊያን “ታሪካዊ መብቶች” በሚል የተሳሳተ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸው አድርጓል ብለዋል።
“ታሪካዊ መብት” የሚለው ሀሳብ ውሃውን ቀድሞ መጠቀም የጀመረ አካል ለዘላለም መቆጣጠር አለበት ከሚል ስግብግብ አስተሳሰብ የመነጨ መሆኑን አመልክተዋል።
ግብጽ በዓለም አቀፍ መድረኮች የምታራምደው የ“ውሃ ደህንነት” ጽንሰ ሀሳብ የዚሁ ጊዜ ያለፈበት የአንድ ወገን የበላይነት ፍላጎት አካል መሆኑንም አቶ ጌታቸው አብራርተዋል።
ይህ ሆን ተብሎ ለፖለቲካዊ ትርፍ የተፈጠረ አሳሳች ትርክት እንደሆነም ነው የተናገሩት።
ግብፅ በዓለም ላይ ደካማ የውሃ አስተዳደር ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት ያሉት አቶ ጌታቸው በበረሃማ አካባቢዎች የሚገኙት እንደ ቱሽካ ያሉ ከፍተኛ የውሃ መጠን የሚጠይቁ ፕሮጀክቶች የዚሁ ብክነት የተሞላበት አጠቃቀም ማሳያ ናቸው ብለዋል።
በግብፅ በሚገኘው የአስዋን ግድብ የሚከሰተው ዓመታዊ የውሃ ትነት መጠን፣ በኢትዮጵያ የውሃ ማከማቻዎች ውስጥ ከሚቀመጠው የውሃ መጠን በእጅጉ የሚበልጥ መሆኑንም ተናግረዋል።
የዓባይ ወንዝ ዋና ምንጭ በሆነችው ኢትዮጵያ እና ሰፊ የመስኖ አቅም ያላት ሱዳን መካከል ሰላም እንዳይኖር ግብፅ ስትሰራ መቆየቷን አንስተው በሱዳን ያለው ቀውስ ሀገሪቱ ውሃውን እንዳትጠቀም ለማድረግ ግብፅ የምታራምደው ስትራቴጂ ነው ብለዋል።
ግብፅ ያላት ብቸኛው መንገድ ጊዜው ያለፈበትን አካሄድ በመተው ከነባራዊው እውነት ጋር መታረቅ መሆኑንም ተናግረዋል።