የእጣንና ሙጫ ደኖችን ለመንከባከብ የማህበረሰብ አቀፍ የደን ጥበቃ ሥራዎች እየተካሔደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የእጣንና ሙጫ ደኖችን ለመንከባከብ የማህበረሰብ አቀፍ የደን ጥበቃ ሥራዎች እየተካሔደ ነው
ገንዳውኃ፣ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ):- የእጣንና ሙጫ ደኖችን በመንከባከብ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የማህበረሰብ አቀፍ የጥበቃ ሥራዎች እየተካሔደ መሆኑን የሰሜን ጎንደር ደንና አካባቢ ጥበቃ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ መልካም ዋሲሁን እንደገለጹት፣ የደን ሀብቱን በመንከባከብ፣ ዘመናዊ የእጣንና ሙጫ አመራረት መንገድን በመከተልና የምርት ጥራትን በመጠበቅ ለገበያ እንዲቀርብ እየተደረገ ይገኛል።
በዋናነትም የእጣንና ሙጫ ደኖችን በመንከባከብና በማልማት ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እንዲቻል የማህበረሰብ አቀፍ የደን ጥበቃ ሥራዎች ላይ በማተኮር እየተሠራ ነው ብለዋል።
በዚሁ መስክ ሥራ አጥ ወገኖችን በማደራጀት ሕገ-ወጥ የደን ጭፍጨፋንና የደን ውጤቶች ዝውውርን በማስቆም ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉንም ነው የተናገሩት።
አምራቾችም ዘመናዊ የምርት አሰባሰብና የአያያዝ ዘዴዎችን በመከተል ጥራት ያለው የእጣንና ሙጫ ምርት ለማቅረብ እንዲችሉ እገዛና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመትም ከሰባት ሺሕ ኩንታል በላይ የእጣን ምርት ለገበያ በማቅረብ ከ374 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።
ከተገኘው ገቢ ውስጥም 74 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የሚሆነው መንግሥት ከሮያሊቲ ክፍያ ገቢ ያደረገው መሆኑን አስረድተዋል።
በዞኑ የሌንጫ አዲስ ሕይወት ሕብረት ሥራ ማኅበር ሊቀመንበር አቶ በየነ ውቤ እንደገለጹት፣ እጣንና ሙጫ በማምረት ሥራ ላይ በማኅበር በመደራጀት ባለፈው ዓመት ወደ ማምረት ሥራ መግባታቸውን ይገልጻሉ።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመትም ማኅበራቸው 362 ኩንታል የእጣንና ሙጫ አምርቶ ለገበያ በማቅረብ ከ21 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ገልጸዋል።
ሌላው በመተማ ወረዳ በመሸሃ ቀበሌ በእጣን ምርት የተሰማሩት አቶ አየነው ሲሳይ፣ በተጠናቀቀው የ2018 ዓ.ም. ከአንድ ሺሕ ኩንታል በላይ እጣን ለገበያ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
በተደጋጋሚ በሚሰጣቸው ሥልጠና አማካኝነት ደኑን ሳይጎዱ ጥራቱን የጠበቀ እጣን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ እንደሚገኙም አስገንዝበዋል።